Fana: At a Speed of Life!

ዘጠኝ የመንገድ መሰረተ ልማት ግንባታ ሊያከናውን መሆኑን የመንገዶች አስተዳደር አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ጥር 28፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ መውጫዎች አካባቢ የሚፈጠሩ የትራፊክ መጨናነቅን መቀነስ የሚያስችሉ ዘጠኝ የመንገድ መሰረተ ልማት ግንባታ ሊያከናውን መሆኑን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር አስታውቋል፡፡

የመንገድ መሰረተ ልማቶቹ ከከተማዋ ወደ ሌሎች አቅጣጫዎች በሚወጡ ተሽከርካሪዎች መጨናነቅ ሳቢያ በሚፈጠር መስተጓጎል በኢኮኖሚው ላይ የሚፈጠረውን ችግር ማስቀረትን ታሳቢ ያደረጉ እንደሆነም ተመላክቷል።

ይሄንን መሰረት በማድረግም ወደ ግንባታ ለመግባት የሚያስችል አስፈላጊው የቅድመ ዝግጅት ስራ መከናወኑ የተገለጸ ሲሆን÷ አሁን ላይም ቅድሚያ የተሰጣቸው መስመሮች ወደ ግንባታ ስራ ገብተዋል ተብሏል፡፡

ከእነዚህም መካከል ከአዲስ – ሆለታ የ14 ነጥብ 7 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው መንገድ ማሻሻያ ፕሮጀክት፣ ከእንጦጦ ማርያም ጉለሌ እጽዋት ማዕከል እንዲሁም የ18 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የእንጦጦ ኮተቤ መንገድ ፕሮጀክት እንደሚገኙበት ተመላክቷል።

በመንገድ ፕሮጀክቶቹ ላይም አስፈላጊ የተባሉ የዲዛይን ማሻሻያዎች ሲደረጉ እንደነበርና ከመንገዶቹ የጎላ ጠቀሜታ አንጻርም የግንባታ ሂደታቸው ደረጃውን ጠብቆ የሚከናወን ይሆናል ነው የተባለው፡፡

በዚህም የአዲስ አበባ ከተማን ከሸገር ሲቲ ጋር ከሚያገናኙ የመንገድ መሰረተ ልማቶች መካከል ግንባታው በቅርቡ ይጀመራል የተባለው የጣፎ አደባባይ-ለገዳዲ-ኩራ-ጂዳ መንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ሲሆን÷ይህም የ17 ኪሎ ሜትር ርዝማኔን የሚሸፍን ፕሮጀክት ነው ተብሏል።

ሁሉም የመንገድ ፕሮጀክቶች የግንባታ ጊዜያቸው በሁለት ዓመት ውስጥ የሚጠናቀቁ መሆናቸውም ተገልጿል።

በይስማው አደራው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.