እስራኤል በቴክኖሎጂ ዘርፍ ለኢትዮጵያ ድጋፏን እንደምታጠክር ገለጸች
አዲስ አበባ፣ ጥር 28፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ከእስራኤል ኢነርጂና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ኢሊ ኮህን ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸውም ሀገራቱ በፈጠራ፣ ቴክኖሎጂ፣ ምርምር፣ ስታርትአፕ ልማትና በሃይል ዘርፍ ያላቸውን ትብብር ማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡
በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ÷ኢትዮጵያ በዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ፣ በስታርትአፕ ልማት፣ በምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በሃይል አቅርቦትና በግብርና ቴክኖሎጂ ጠንካራ እንቅስቃሴ እያደረገች ነው ብለዋል፡፡
በተለይም ዲጂታል ኢትዮጵያ እውን ማድረግ የሚያስችሉ ሥራዎችን እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመው ÷ እስራኤል በዘርፉ ያላትን ጠንካራ ልምድ በተሞክሮነት የሚወሰድ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ኤሊ ኮህን በበኩላቸው ÷ በግብርና ቴክኖሎጂ፣ በኢኖቬሽንና በታዳጊ የቴክኖሎጂ መስኮች ያለውን ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ መስራት እንደሚገባ አንስተዋል፡፡
እስራኤል በቴክኖሎጂና በሃይል ያላትን እውቀት በመጠቀም እያደገ የመጣውን የኢትዮጵያ የኢኖቬሽን ሥነ-ምህዳር ለመደገፍና ዝግጁ መሆኗን አረጋግጠዋል፡፡
ውይይቱ የእስራኤል ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች ኢንቨስት እንዲያደርጉ በር የሚከፍት እንደሆነ መናገራቸውንም የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡