Fana: At a Speed of Life!

“የደህንነት አባል ነኝ” በማለት በሃሰተኛ ሰነድ ከባለሃብት ከ13 ሚሊየን ብር በላይ የወሰደው ተከሳሽ በ14 ዓመት ጽኑ እስራት ተቀጣ

አዲስ አበባ፣ ጥር 28፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የብሔራዊ መረጃ ደህንነት ሰራተኛ ነኝ በማለት ለሲሚንቶ ፋብሪካ ቦታ ጉዳይ ማስፈጸሚያ ከአንድ ባለሃብት ከ13 ሚሊየን ብር በላይ ገንዘብ የወሰደው ግለሰብ በ14 ዓመት ጽኑ እስራትና በገንዘብ እንዲቀጣ ተወሰነ፡፡

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ቱጁባ ቶልቻ ሰንበታ በተባለ ተከሳሽ ማስረጃ መዝኖ ዛሬ ረፋድ በነበረ ቀጠሮ በቀረበበት የሙስና ወንጀል ክስ የ14 ዓመት ጽኑ እስራትና የገንዘብ መቀጮ ውሳኔ ሰጥቷል።

የፍትህ ሚኒስቴር የሙስና የወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጄነራል ዐቃቤ ሕግ ተከሳሹ ነዋሪነቱ በአዲስ አበበ ከተማ ቦሌ ክ/ከተማ ወረዳ 12 የነበረ መሆኑን ጠቅሶ ፤ የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 28(3) ላይ እና አንቀጽ 23 ንዑስ ቁጥር (1)፤ (2) እና (3) እንዲሁም  በወንጀል ድርጊት የተገኘን ገንዘብ ወይም ንብረት ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብን እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 780/2005 አንቀጽ 29 ንዑስ ቁጥር 1 (ሀ)(ለ)(ሐ) ስር የተመላከቱ ድንጋጌዎችን አመላክቶ ባሳለፍነው 2016 ዓ.ም  ዝርዝር ክስ አቅርቦበት ነበር።

በዚህም በቀረበ ዝርዝር ክስ ላይ እንደተመላከተው ተከሳሹ በነሐሴ ወር 2015 ዓ.ም የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት ሠራተኛ ሳይሆን ” ደህንነት ነኝ ” በማለት ባለሃብቶችን በመተዋወቅና በመቅረብ ከፍተኛ የፌዴራል እና የክልል ባለስልጣናትን እንደሚያውቅ ለግል ተበዳይ ለሆኑት አኪል አባስ ለተባሉ ግለሰብ በመግለጽ፣ ግለሰቡ ሊሰሩ ላሰቡት የሲሚንቶ ፋብሪካ ፈቃድ እና የግንባታ ቦታ ለማግኘት እንዲችሉ የፕሮጀክት ፕሮፖዛል አዘጋጅቶ ለሚመለከታቸው የክልል እና የፌደራል የመንግስት ተቋማት ጥያቄ ከማቅረብ ጀምሮ እስከ ግንባታ ቦታ ካርታ መረከብ ያለውን ሙሉ ሂደት አስጨርሶ እንደሚያስረክባቸው መግለጹ በክሱ ላይ ተመላክቷል።

በዚህ መልኩ ለስራ ማስኬጃ በማለት ከግል ተበዳይ ነሐሴ 5 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ ቀናት በስሙ በተከፈተው የኢትዮጲያ ንግድ ባንክ ሂሳብ እና በአዋሽ ባንክ ሂሳብ በአጠቃላይ 13 ሚሊየን 180 ሺህ  ብር ገቢ እንዲሆንለት ማድረጉ በክሱ ዝርዝር ላይ ተጠቅሷል።

ከዚህም በኋላ ተከሳሹ በአሊፍ ግሎባል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማህበር ስም በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ሰሜን ሸዋ ዞን ያያ ጉለሌ ወረዳ የሲሚንቶ ፋብሪካ ግንባታ ፍቃድ እንዲሰጠው ለክልሉ የማዕድን ልማት ባለስልጣን እና ለፌዴራል ማዕድን ሚኒስቴር ምንም ጥያቄ ባላቀረበበት ሁኔታ ላይ  “ጥያቄ አቅርቤ ፕሮጀክቱ ተቀባይነት አግኝቷል ፣ ቦታውም ተፈቅዷል ” በማለት በጥቅምት 24 ቀን 2016 ዓ.ም ከቀኑ 4 ሰዓት ገደማ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከተማ ሳር ቤት ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ሃሰተኛ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ሰሜን ሸዋ ዞን ማዕድን ልማት ባለስልጣን ክብ ማህተብ ያለበት ቅድመ ካርታና ሌሎችም ሀሰተኛ ሰነዶችን ለግል ተበዳይ  የሰጠ መሆኑ በክሱ ዝርዝር ላይ  ተመላክቷል።

በተጨማሪም ተከሳሹ  በፈጸመው በሙስና ወንጀል ምክንያት ያገኘው ገንዘብ የወንጀል ፍሬ መሆኑን እያወቀ የገንዘቡን ሕገ-ወጥ ምንጭ ለመደበቅ እና ከሕግ ተጠያቂነት ለማምለጥ በማሰብ በተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ መጠኖች በሕገ-ወጥ ተግባር ካገኘው ገንዘብ ውስጥ 5 ሚሊየን 154 ሺህ ብር በላይ ለሌሎች ግለሰቦች በማስተላለፍ ምንጩን የደበቀ መሆኑ ተጠቅሶ ፤ በወንጀል ድርጊት የተገኘን ገንዘብን ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብ ወንጀል ተከሷል፡፡

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የክትትል ቡድን አባላት ተከሳሹን በቁጥጥር ስር አውሎ ፍርድ ቤት ካቀረበው በኋላ የተመሰረተበት ክስ ዝርዝር እንዲደርሰውና በንባብ እንዲሰማ ተደርጓል።

ተከሳሹ በክሱ ላይ የተጠቀሰውን የወንጀል ድርጊት አለመፈጸሙን ጠቅሶ የሰጠውን የዕምነት ክህደት ቃል ተከትሎ ዐቃቤ-ሕግ የሰውና የሰነድ ማስረጃ አቅርቦ አሰምቷል።

በወቅቱ መዝገቡን ሲመለከቱ የነበሩ የችሎቱ ዳኞች የዐቃቤ ሕግ ማስረጃኝ መርምረው ተከሳሹን በ2ኛ እና በ3ኛ ክስ ማለትም በሙስና አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 28 /3 ሥር እንዲሁም እና አንቀጽ 29 (1) (ሀ) (ለ) እና (ሐ) ሥር እንዲከላከል ብይን በመስጠት ተከሳሹ በ300 ሺህ ብር ዋስ አስይዞ ከእስር እንዲፈታ ትዕዛዝ ተሰጥቶ ከእስር ተፈቶ ነበር።

ከዚህም በኋላ ፍርድ ቤቱ በየጊዜው በሚያደርገው የዳኞች የችሎት ዝውውር መሰረት ሌሎች ዳኞች ተቀይረው መዝገቡን ተረክበው ማስረጃ መርምረውና መዝነው ተከሳሹ ላይ  የጥፋተኝነት ፍርድ ተሰጥቷል።

ዛሬ በዋለው የችሎት ቀጠሮ ደግሞ የቅጣት አስተያየት ተመርምሮ በቅጣት አወሳሰን መመሪያ ቁጥር 2/2006 አንቀጽ 19 ንዑስ ቁጥር (2) መሠረት ደረጃውን ከባድ በማለት በሁለቱም ክሶች ተከሳሹ በ14 ዓመት ጽኑ እስራትና በ40 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ ተወስኗል።

በተጨማሪም ተከሳሹ ፍርድ ቤት ያልቀረበ ስለሆነ በሙስና ወንጀሎች አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 6 መሰረት ለእያንዳንዱ ጥፋተኛ ለተባለበት በድምሩ 280 ሺህ ብር ገንዘብ እንዲከፍል ተወስኖበታል።

በሌላ በኩል ቀደም ሲል ተከሳሹ በዋስትና ያስያዘው 300 መቶ ሺህ ብር ለመንግስት ገቢ እንዲሆን መወሰኑ ተመላክቷል፡፡

የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ተከሳሹን አፈላልጎ በመያዝ የተወሰነበትን ጽኑ እስራት እንዲያስፈጽም ለማረሚያ ቤት እንዲያስረክብ ትዕዛዝ ተሰጥቷል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.