ምክር ቤቱ ሁለት አዋጆችን አፀደቀ
አዲስ አበባ፣ ጥር 29፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው 18ኛ መደበኛ ስብሰባ የፌዴራል የፍትህና የህግ ኢንስቲትዩት እንዲሁም የሲቪል እና የቤተሰብ ምዝገባ ስርዓት አዋጆችን መርምሮ አጽድቋል፡፡
የፌዴራል የፍትህና የህግ ኢንስቲትዩትን እንደገና ለማቋቋም በህግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ለምክር ቤቱ የቀረበው ረቂቅ አዋጅ አዋጅ ቁጥር 1000 /369/2017 ሆኖ በሙሉ ድምጽ ፀድቋል፡፡
ዘመናዊ ቴክኖሎጂን ማዕከል ያደረገ ጥናትና ምርምር በማድረግ የዳኝነትና የፍትህ ስርዓቱን ማዘመን፣ ህጎችን ከወቅታዊው የዓለምና የሀገሪቱ የእድገት ደረጃ እንዲጣጣም ለማድረግ ጠንካራ የህግና ፍትህ ኢንስቲትዩት ማቋቋም አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱም አዋጁ ወጥቷል ተብሏል፡፡
በተጨማሪም ምክር ቤቱ የሚወጡ አዋጆች ላልተፈለገ አላማ እንዳይውሉና ጥንቃቄ እንዲደረግ በማሳሰብ የሲቪል እና የቤተሰብ ምዝገባ ስርዓትን ለመደንገግ የወጣ ረቂቅ አዋጅን መርምሮ አዋጁን በሙሉ ድምጽ አፅድቋል፡፡
እንዲሁም ምክር ቤቱ የአካባቢና ማህበራዊ ተፅዕኖ ግምገማ ረቂቅ አዋጆችን አስመልክቶ የሚቀረበውን ሪፖርትና የውሳኔ ሀሳብ መርምሮ ያፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል።
በየሻምበል ምህረት