Fana: At a Speed of Life!

መከላከያ የዲጂታል ሽግግር ሂደትን አጠናክሮ ይቀጥላል- ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

አዲስ አበባ፣ ጥር 29፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) መከላከያ የዲጂታል ሽግግር ሂደትን አጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ የጦር ሀይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለጹ፡፡

በመከላከያ ሠራዊት ፋውንዴሽን የቤት ማስተላለፍና ማስተዳደር ምዝገባ አዲስ ሶፍትዌር መተግበሪያን አስመልክቶ የተካሄደው ሥልጠና ተጠናቅቋል።

በማጠቃለያው መድረክ የተገኙት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ÷ዓለም በቴክኖሎጂ ብዙ ተግባራትን በማከናወን ላይ ነው ሀገራችንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ዘርፉን በመተግበር ላይ ትገኛለች ብለዋል።

የመከላከያ ሠራዊት ፋውንዴሽንም በዓድዋ ድል ማይክሮ ፋይናንስ አክስዮን ማህበር፣ በግብርና፣ በኢንዱስትሪ ምርቶች እና በሌሎች ዘርፎች ያለውን ውጤታማ እንቅስቃሴ ማጠናከር እንደሚገባው አሳስበዋል።

መከላከያ ዲጂታል ቴክኖሎጂን በመጠቀም ተልዕኮዎችን በመፈፀም ውጤታማ እንቅስቃሴ እያካሄደ ነው ያሉት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ፥ ቀጣይም ከባለድርሻ አካላት ጋር የዲጂታል ሽግግርን የሚያጠናክሩ ተግባራትን ይሠራሉ ሲሉ ተናግረዋል።

ፋውንዴሽኑ ተቋሙ በሚሰጠው አቅጣጫ መሠረት የሠራዊቱን ማህበራዊ ኑሮ ለማሻሻል ጠንክሮ መሠራቱንና አዲሱ የሶፍትዌር መተግበሪያ ተልዕኮዎችን በዲጂታል ቴክኖሎጂ በውጤት ለመፈፀም ያለመ መሆኑን የመከላከያ ሠራዊት ፋውንዴሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ ብርጋዲየር ጄኔራል ደረጀ መገርሳ ገልፀዋል።

አዲሱ መተግበሪያ በመከላከያ ኢንፎርሜሽን ኮሚዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ማዕከል በመበልፀጉ ከ67 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ ማስቀረት መቻሉንም ከመከላከያ ሠራዊት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.