የአዲስ አበባ ከተማ ካቢኔ በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ውሳኔ አሳለፈ
አዲስ አበባ፣ ጥር 29፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ በ4ኛ ዓመት 7ኛ መደበኛ ስብሰባው በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል።
በከተማ አስተዳደሩ በጀት ተመድቦላቸው የተገነቡ እና በመጠናቀቅ ላይ ያሉትን አዳዲስ ሆስፒታሎች ዘመኑን በዋጀ ህክምና መሳሪያ ለማሟላት እና ዓለም አቀፍ ደረጃን የሚያሟላ አገልግሎት መስጠት ያስችላቸው ዘንድ በዘርፉ ትልቅ ልምድ ካካበቱ የግል ሴክተር ጋር በአጋርነት ለመስራት ውሳኔ አሳልፏል።
አንዳንድ የመንግስት አገልግሎቶችን በውል ለ3ኛ ወገን ለማሰራት የወጣውን ረቂቅ ደንብ መርምሮ በማየት ካቢኔው ማፅደቁን የከንቲባ ጽሕፈት ቤት መረጃ ያመለክታል።
እንዲሁም የተለያዩ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ላላቸው እና ተኪ ምርቶችን ለሚያመርቱ ኢንዱስትሪዎች ባቀረቡት የማስፋፊያ ቦታ ጥያቄዎች ላይ በጥልቅ በመወያየት እና የአተገባበር አቅጣጫ በማስቀመጥ በሙሉ ድምፅ አፅድቋል።
የኮሪደር ልማት ውጤት ከሆኑት ሥራዎች አንዱ የብዙሃን ትራንስፖርት መሠረተ ልማት ችግሮች የሚያቃልል እና የትራፊክ ፍሰቱን የሚያሻሽለው የብስክሌት መጋራት አገልግሎት እና የብስክሌት መስመር አጠቃቀም ደንብን በመመርመር አፅድቋል።