Fana: At a Speed of Life!

ሆን ተብሎ በሰው አማካይነት 10 የቃጠሎ አደጋዎች ደረሱ

 

አዲስ አበባ፣ ጥር 30፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ባለፉት 6 ወራት በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የደረሱ 103 የእሳት ቃጠሎ መንስኤዎችን በፎረንሲክ ምርመራ አጣርቶ ውጤቱን ይፋ አድርጓል ።

በምርመራው በአዲስ አበባ ከተማ የተከሰቱ 96 እንዲሁም በክልሎች ሰባት የእሳት ቃጠሎ አደጋዎች መንስኤዎች ይፋ መደረጋቸው ተጠቁሟል፡፡

በዚህ መሰረትም በኤሌክትሪክ ቴክኒክ ችግር ምክንያት የደረሰ 50 ቃጠሎ፣ በመካኒካል ችግር ምክንያት የደረሰ 11 ቃጠሎ፣ ሆን ተብሎ በሰው አማካኝነት የደረሰ 10 ቃጠሎ፣ በቸልተኝነት የደረሰ 17 እና በሌሎች ምክንያቶች የደረሰ 15 ቃጠሎ መሆናቸውን አረጋግጧል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ጥቅምት 11 ቀን 2017 ዓ.ም ምሽት በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ሸማ ተራ ነባር የገበያ ማዕከልና በአካባቢው የደረሰው የእሳት አደጋ መንስኤ በኤሌክትሪክ ቴክኒክ ችግር የተከሰተ አደጋ መሆኑን በፎረንሲክ ምርመራ ማጣራት መቻሉ ተገልጿል፡፡

በግማሽ ዓመቱ በ582 መኖሪያ ቤት፣ በ12 ተሽከርካሪዎች፣ በ1 ሺህ 965 ንግድ ቤቶች በስድስት ፋብሪካዎችና የተለያዩ ድርጅቶች በቃጠሎ ምክንያት ጉዳት ስለመድረሱ ሪፖርቱ አመላክቷል።

ኅብረተሰቡ ቃጠሎ ከደረሰ በኋላ ማስረጃዎች ሳይነካኩ መጠበቅና ለፖሊስ ሪፖርት ማድረግ እንዳለበት እንዲሁም የቃጠሎ መንስኤዎች በሙያዊ ምርመራ እስካልተረጋገጡ ድረስ አስተያየት መስጠትና መፈረጅ ፍትሕን ስለሚያዛባ ከዚህ እንዲቆጠብ ፖሊስ አሳስቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.