Fana: At a Speed of Life!

ከ8 ማሊየን ብር በላይ ከአንድ ግለሰብ በማታለል የወሰዱ በ9 ዓመት ጽኑ እስራት ተቀጡ

አዲስ አበባ፣ ጥር 30፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ”2 ሺህ ካሬ ሜትር ይዞታ ለማሰጠት” በሚል ከ8 ማሊየን ብር በላይ ከግለሰብ አታልለው የወሰዱ ግለሰቦች በዘጠኝ ዓመት ጽኑ እስራት ተቀጡ።

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት በከባድ የማታለል ሙስና ወንጀል በተከሰሱ ዘላለም አስራት እና ዘካሪያስ ሙላቱ በተባሉ ተከሳሾች ላይ የቀረቡ ማስረጃዎችን መርምሮና አመዛዝኖ ዛሬ ረፋድ በነበረ ቀጠሮ የጽኑ እስራትና የገንዘብ የቅጣት ውሳኔ አስተላልፏል።

የፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ወንጀሎች ዳይሬክቶሬት ጄነራል ዓቃቤ ህግ በተከሳሾቹ ላይ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢፌዴሪ ወንጀል ሕግ አንቀጽ 32(1) (ሀ) (ለ)33 እና የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣው አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 32 (2) እና በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብን እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 780/2005 አንቀጽ 29 (1) ስር የተመለከተውን ድንጋጌ በመተላለፍ የሚል ዝርዝር ክስ በ2016 ዓ/ም አቅርቦባቸው ነበር።

በዚህም ቀርቦ በነበረ ክስ ላይ እንደተመላከተው 1ኛ እና 2ኛ ተከሳሽ በግል ስራ የሚተዳደሩ ሆነው ሲሰሩ የማይገባቸዉን ብልፅግና ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰዉ ለማስገኘት በማሰብ የካቲት 2015 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቂርቆስ ክ/ከተማ ድሪም ላይን ሆቴል ውስጥ የናይል ቢዝነስ ግሩፕ ኃ/የተ/የግ/ማህበር የበላይ ሥራ አስፈፃሚ የሆኑት አቶ ተመስገን መሃሪ በ1991ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር ቂርቆስ ክ/ከተማ ወረዳ 09 በቀድሞ 18 ቀበሌ 26 ቦሌ መንገድ ከሞቢል ነዳጅ ማደያ አጠገብ ለቢሮ አገልግሎት ግንባታ የሚሆን 2 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጽ/ቤት እንዲሰጠዉ ተወስኖ የነበረዉን በጊዜዉ ባለመረከባቸው መነሻ በማድረግ 2ኛ ተከሳሽ ይህንን ጉዳይ ተከታትሎ የሚያስፈፅምላቸዉ ሰው አውቃለዉ በማለት 1ኛ ተከሳሽን በመጥራት ያስተዋወቃቸው መሆኑን ዐቃቤ ህግ በክሱ ጠቅሷል።

1ኛ ተከሳሽ ”እኔ ብዙ ሰዉ አውቃለሁ ፤ ጉዳዩን አስጨርሳለዉ” በማለት ከድርጅቱ መጋቢት 8 ቀን 2015ዓ.ም ውክልና በመውሰድ ለቂርቆስ ክፍለ ከተማ መሬት ልማት አስተዳደር ቢሮ ቀድሞ በተወሰነው መሰረት ይፈፀም የሚል በተቋሙ የማይታወቅ በሃሰት የተዘጋጀን ደብዳቤ ከከንቲባ ጽ/ቤት አስወስነናል በማለት ለግል ተበዳይ የሰጠ መሆኑ ተመላክቷል።

ግንቦት 3 ቀን 2015 ዓ.ም ደግሞ በቂርቆስ ክፍለ-ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማትና አስተዳደር ጽ/ቤት ተመሳስሎ የተፃፈ ‘የሊዝ ውል እንዲዋዋሉ እና የሊዝ ክፍያ እንዲፈፅሙ ” የሚል በተቋሙ የማይታወቅ በሃሰት የተዘጋጀን ደብዳቤ በማሳየት ቀርበዉ የሊዝ ውል እንዲዋዋሉ ለግል ተበዳዮቹ በመግለጽ ሃሰተኛ የሊዝ ውል ፎርም በማዘጋጀት ውል ተቀባይ ቦታ ላይ 1ኛ የዓ/ህግ ምስክር የሆኑት የግል ተበዳይን ስም ፅፈዉ እንዲፈርሙ በማድረግ ፣ በውል ሰጪ ቦታ ላይ ደግሞ ”የተቋሙን ሃላፊ አስፈርመን ቀሪ የሊዝ ውል ትወስዳላቹ ፤ ክፍያዉን ክፈሉ” ብሎ በማታለል ወንጀል መፈጸማቸው ተጠቅሶ በክሱ ተመላክቷል።

እንደ አጠቃላይ ”ለሊዝ የሚከፈል” በሚል በንግድ ባንክ፣ አዋሽና አቢሲንያ ባንክ በተለያዩ መጠኖች ገንዘብ ገቢ እንዲደረግላቸው በማድረግ እና በክፍለ ከተማዉ የማይታወቅ ሃሰተኛ ደረሰኝ የተወራረደ በማስመሰል ሃሰተኛ የገቢ ደረሰኝ ሰነድ ለግል ተበዳይ ተከሳሾች ከናይል ቢዝነስ ግሩፕ ኃ/የተ/የግ/ማህበር የበላይ ሥራ አስፈፃሚ ከሆኑት አቶ ተመስገን መሃሪ 8 ሚሊየን 300 ሺህ ብር በማታለል የወሰዱ እና ገንዘቡንም ምንጩን ለመሸሸግ በተለያዩ ሰዎች ስም በተከፈተ ባንክ ሂሳብ ማስተላለፋቸው በክስ ዝርዝሩ ላይ ተጠቅሶ ፤ በዋና ወንጀል አድራጊነትና ተካፋይነት ከባድ አታላይነት የሙስና ወንጀል ክስ ቀርቦባቸው ነበር።

ተከሳሾቹ ፍርድ ቤት ቀርበው ክሱ ከደረሳቸው በኋላ የወንጀል ድርጊት አለመፈጸማቸውን ጠቅሰው ፥ የእምነት ክህደት ቃላቸውን መስጠታቸውን ተከትሎ ፍርድ ቤቱ ዐቃቤህግ ያቀረበውን የሰው ምስክርና የሰነድ ማስረጃ መርምሮ እንዲከላከሉ ብይን ሰጥቷል፡፡

ተከሳሾቹም ያቀረቡትን የተለያዩ መከላከያ ማስረጃዎች ተመርምሮና ከዐቃቤ ህግ ማስረጃ ጋር ተመዝኖ ዐቃቤ ህግ በማስረጃ እና በተገቢው መከላከል አለመቻላቸውን ጠቅሶ የጥፋተኝነት ፍርድ አስተላልፎባቸዋል።

በተለይም በዚሁ መዝገብ በ3ኛ ተከሳሽነት አብሮ ተከሶ የነበረው የቀድሞ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቂርቆስ ክ/ከተማ የመሬት ይዞታ ምዝገባ እና መረጃ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የፕላን ፣ ትመና እና ምህንድስና ከፍተኛ ባለሙያ የነበረው ሄኖክ ዘሪሁን ይርጋን በሚመለከት የዐቃቤ ህግ ማስረጃን ማስተባባሉ ተጠቅሶ ከቀረበበት ክስ ነጻ ነው ተብሎ ብይን ተሰጥቷል።

ከዚህ በኋላ ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኝ የቅጣት አስተያየት በመመርመር 1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች ያቀረቡትን አምስት አምስት የቅጣት ማቅለያ አስተያየትን በመያዝ እንዲሁም ዐቃቤ ህግ ወንጀሉ በትብብር የተፈጸመ መሆኑን ጠቅሶ ያቀረበውን አንድ የቅጣት ማክበጃን በመያዝ በእርከን 28 ስር እያንዳንዳቸው ተከሳሾችን በ9 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ተወስኗል።

የገንዘብ መቀጮውን በሚመለከት ደግሞ በእርከን 7 ስር እያንዳንዳቸው በ10 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ ተወስኗል።

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.