እንግሊዝ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ትብብር እንደምታጠናክር ገለጸች
አዲስ አበባ፣ ጥር 30፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ የእንግሊዝ አምባሳደር ዳረን ዌልች ጋር ተወያይተዋል።
በውይይታቸውም በማህበራዊ ጥበቃና አካታችነት፣ በሴቶች መብትና ሥርዓተ ጻታ እኩልነት እንዲሁም የሴት ልጅ ግርዛትንና ጾታን መሠረት ያደረገ ጥቃትን መከላከል በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መክረዋል፡፡
ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ÷በማህበረሰቡ ዘንድ ያለው የተዛባ አመለካከት፣ የመረጃ እጥረትና የሃብት ውስንነት የሥርዓተ ጾታ እኩልነት እንዳይሰፍን ማድረጉን ተናግረዋል፡፡
ችግሩን ለመፍታት በጋራ መስራት እንደሚያስፈልግ መግለጻቸውንም የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡
የእንግሊዝ መንግስት ቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በኢትዮጵያ በዘርፉ ለሚከናወኑ ሥራዎች ለሚያደርገው ድጋፍም ምስጋና አቅርበዋል።
አምባሳደር ዳረን ዌልች በበኩላቸው፥ እንግሊዝ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን አጋርነት ይበልጥ ለማጠናከር እና በተለያዩ ዘርፎች በትብብር ለመሥራት እንደምትፈልግ አረጋግጠዋል፡፡