Fana: At a Speed of Life!

ፓኪስታን ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ኢኮኖሚያዊ አጋርነት እንደምታጠናክር አስታወቀች

አዲስ አበባ፣ ጥር 30፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮ-ፓኪስታን ኤግዚቢሽን እና 5ኛው የፓኪስታን አፍሪካ የንግድ ልማት ኮንፈረንስ የፊታችን ግንቦት ወር አጋማሽ ላይ ይካሄዳል፡፡

ኮንፈረንሱን አስመልክቶ የሁለቱም ሀገራት የንግድ ማህበረሰብ እና ሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣናት በተገኙበት የማስተዋወቂያ መርሐ ግብር ተካሂዷል፡፡

በመድረኩ ንግግር ያደረጉት የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ ያስሚን ወሃብሬቢ÷መጪው አህጉራዊ ኮንፈረንስ የንግድ ግንኙነቱን ለማጠናከርና በሀገራቱ መካከል ያለውን ትብብር ለማሳደግና አዳዲስ የንግድ ዕድሎችን እንደሚፈጥር ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ የፓኪስታን አምባሳደር አቲፍ ሸሪፍ ሚያን በበኩላቸው÷ባለፉት አምስት ዓመታት የሁለቱ ሀገራት የሁለትዮሽ ንግድ በ132 በመቶ ማደጉን ገልጸዋል።

በተለይ ኢትዮጵያ ወደ ፓኪስታን የምትልከውን ምርት በብዙ እጥፍ ጨምሯል፤ፓኪስታን ወደ ምስራቅ አፍሪካ የምትልከው ምርትም በ40 በመቶ ከፍ ብሏል ብለዋል።

ፓኪስታን ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የምጣኔ ሀብት ትብብር እና የንግድ ዘርፎችን ለማስፋት ፍላጎት እንዳላት ገልጸው÷ወደ ኢትዮጵያ የምትልካቸውን ምርቶች ለማሳደግ ፍላጎት መኖሩን አመልክተዋል።

አምባሳደር ሚያን ኢትዮጵያ በአህጉሪቱ የፓኪሰታን ቁልፍ አጋር እንደሆነች ነው አጽንኦት የሰጡት፡፡

ፓኪስታን የደቡብ-ደቡብ ትብብርን ለማጉላት ፍላጎት እንዳላት የገለጹት አምባሳደሩ÷በሀገራቸው የሚገኙ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት በኢትዮጵያ ውስጥ ተግባራዊ ፕሮጀክቶችን በመቅረፅ በተለያዩ ዘርፎች መዋዕለ ንዋያቸውን ለማፍሰስ እንዲችሉ ኤምባሲው እያበረታታ ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ የፓኪስታን ኤምባሲ የንግድ እና ኢንቨስትመንት ሚኒስትር ባሲት ሳሌም ሻህ በበኩላቸው÷ሀገራቸው ፓኪስታን ከ240 ሚሊየን በላይ ዜጎች መኖሪያ መሆኗን ገልጸው ይህም ለኢትዮጵያ ቡና ትልቅ ወጪ ንግድ ሰፊ እድል ይፈጥራል ብለዋል።

ስለሆነም የሁለቱን ሀገራት ምጣኔ ሃብታዊ ትስስር ለማሳደግ አሁንም ሰፊ ስራዎች መስራት እንደሚገባ ነው ያስገነዘቡት፡፡

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.