የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር መስመር በሙሉ አቅሙ አገልግሎት እንዲሰጥ የሚያስችል ምክክር ተደረገ
አዲስ አበባ፣ ጥር 30፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የትራንስፖርት እና ሎጂስክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ቺን ሀይ ከተመራ የቻይና ብሔራዊ ባቡር አስተዳደርና ኮሙኒኬሽንስ ኮንስትራክሽን ካምፓኒ ተወካዮች ጋር ተወያዩ፡፡
በውይይታቸው የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር መስመር በሙሉ አቅሙ አገልግሎት እንዲሰጥ ለማስቻል በትብብር ሊሰሩ ስለሚችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡
ዓለሙ ስሜ(ዶ/ር) በውይይቱ ÷የኢትዮ ጅቡቲ ባቡር መስመር ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታትና መስመሩን በሙሉ አቅም ለመጠቀም ከክልል መንግስታት ጋር በቅንጅት እየሰራን ነው ብለዋል፡፡
በመስመሩ የሰውና እንስሳት መሸጋገሪያ አለመኖር በባቡሩ ፍጥነትና የማጓጓዝ አቅም ላይ ተፅዕኖ ማሳደራቸውን ጠቁመው የመሸጋገሪያ ድልድዮችን መገንባትና አጥር ማጠር ችግሩን በዘላቂነት የሚፈታ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ኢትዮጵያ ያላትን የወጪ ገቢ ጭነት ፍላጎት ለማሟላት የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር መስመርን ከሌሎች ኮሪደሮች ጋር የማገናኘትና አዳዲስ መስመሮችን በመገንባት የሀገሪቱን የሎጂስቲክስ ቅልጥፍና ለማሳደግ እየሰራን ነው ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ቺን ሀይ ÷የባቡር መስመሩ ደህንነቱ ተጠብቆ ዘላቂና ውጤታማ አገልግሎት እንዲሰጥ ለማድረግ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በትብብር መስራት እንደሚፈልጉ ገልጸዋል፡፡
የልዑካን ቡድኑ ችግሮችን ለመፍታትና የባቡር መስመሩን ውጤታማነት ለማሳደግ በጋራ ለመስራት ቁርጠኝነታቸውን መግለፃቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡