ከ641 ሚሊየን ብር በላይ ወጭ ሁለት የመጠጥ ውሃ ልማት ስምምነቶች ተፈረሙ
አዲስ አበባ፣ ጥር 30፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከ641 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጭ የመጠጥ ውሃ ግንባታ እና የማማከር ኮንትራት አስተዳደር ስራዎች የውል ስምምነቶችን ፈረመ ።
የመጀመሪያው ስምምነት የተፈረመው በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር እና የሰርጃ የግንባታና አጠቃላይ የንግድ ስራዎች ፒ ኤል ሲ እና ቢጌታ ቢዝነስ ፒኤል ሲ በጋራ በመሆን ነው።
በሚኒስቴሩ ስር በዋን ዎሽ ፕሮግራም የሚተገበረው የባለብዙ መንደር የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት አካል የሆነውና በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ጣርማ በር ወረዳ የአጋም በር የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ግንባታ የእቃ አቅርቦትን ጨምሮ ከ631 ሚሊየን ብር በላይ ወጭ እንደሚደረግበት ታውቋል።
የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቱ ከ21 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ሲሆን በ18 ወራት ውስጥ ተገንብቶ እንደሚጠናቅም የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡
በሌላ በኩል በሚነስቴሩ እና በሲዳማ ዲዛይንና ግንባታ ቁጥጥር ኢንተርፕራይዝ መካከል በአዋሳ ዙሪያ ወረዳ ለሚገነባው የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት የማማከርና ኮንትራት አስተዳደር ስራዎችን ለመስራት የሚያሰችል ስምምነት ተፈርሟል።
የማማከርና ኮንትራት አስተዳደር ስራው በ15 ወራት የሚተገበር ሲሆን ከ10 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ወጭ እንደሚጠይቅ ተገልጿል።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ(ዶ/ር) ከስምምነቱ በኋላ እንደገለጹት ፕሮጀክቶቹ በተቀመጠው ጊዜ በጥራት ተገንብተው የህብረተሰቡን የመጠጥ ውሃ ፍላጎት እንዲያሟሉ ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል።