Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ሰላምና መረጋጋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተች ነው – አምባሳደር ዲና ሙፍቲ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ሰላምና መረጋጋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተች መሆኗን በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ተናገሩ።

አምባሳደሩ የኢትዮጵያ ሰላም ለጎረቤቶቿ ሰላም ወሳኝ እንደመሆኑ መጠን የጎረቤት ሀገራትም ሰላም የራሷ ሰላም መሆኑን በተግባር አረጋግጣለች ብለዋል።

ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ነጻነት ያበረከተችውን አስተዋጽኦ ያህል ለአፍሪካ ሰላምና መረጋጋትም ሚናዋን እየተወጣች ያለች ሀገር መሆኗን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ለሶማሊያ ሰላምና መረጋጋት ያደረገችው አስተዋጽኦ ለዓለም ሰላም ጭምር እንዳደረገችው የሚወሰድ መሆኑን ገልጸዋል።

የአፍሪካ ሀገራት ለሽብርተኝነት ሽፋን ሊሆኑ የሚችሉ ሁኔታዎችን ማረም እንደሚገባቸው ጠቁመው፤ ይህም ለአካባቢው ሀገራት የልማት፣ የእድገት እንዲሁም የሰላም ማረጋገጫ ምቹ መንገድ የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል።

አምባሳደሩ አክለውም በቀጣናው ሠላም እንዲሰፍን ሀገራት ሽብርተኝነትን ለመከላከል በጋራ የሚያደርጉት ጥረት ዓለም አቀፍ ግንኙነታቸው ይበልጥ እንዲጠናከር እንደሚያስችል አንስተዋል።

ሰላምን በማወክ የአካባቢውን ሀገራት እድገት ወደ ኋላ ሊያስቀር የሚችለውን ሽብርተኝነትን ለማጥፋት በጋራ መንቀሳቀስ አለባቸው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ኢትዮጵያ ከዚህ በፊትም ከወዳጅ ሀገራት ጋር በመተባበር ሰፋፊ ተግባራትን ስታከናውን መቆየቷንም ጠቁመዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.