Fana: At a Speed of Life!

በ1 ቢሊየን ብር ወጪ የተገነባው የፕላስቲክ ፎርምዎርክ ፋብሪካ ተመረቀ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ከ1 ቢሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባውን የፕላስቲክ ፎርምወርክ ፋብሪካ መርቀው ሥራ አስጀምረዋል።

ፋብሪካው ገቢ ምርትን በመተካት በዓመት ከ15 ሚሊየን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ የማዳን አቅም እንዳለው ተገልጿል።

አቶ መላኩ አለበል በዚሁ ወቅት እንዳሉት÷ለአምራች ኢንዱስትሪ በልዩ ትኩረት የፖሊሲ እና የህግ ማእቀፎችን በማሻሻል ውጤታማ ስራዎች እየተከናወኑ ነው፡፡

ለዘርፉ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እና ክትትል በማድረግ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የተረጋጋ ኢኮኖሚ ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

ምርት ለውጭ ገበያ የሚያቀርቡ ጠንካራና ተወዳዳሪ ኢንዱስትሪ መገንባት የሚቻለው ወደ ሀገር የሚገባ ምርትን የሚተኩ ኢንዱስትሪዎችን በመደገፍ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ዛሬ የተመረቀው ፋብሪካም ተኪ ምርትን በማስፋትና የሀገራዊ ፖሊሲን በማሳጋት ረገድ ትልቅ ሚና እንደሚኖረው አንስተዋል።

ፋብሪካው በሀገራችን የእንጨት ፎርምዎርኮችን በፕላስቲክ መተካት መቻሉ ኢትዮጵያ የጀመረችውን የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ከመደገፍ አኳያ ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ጠቁመዋል።

በተለይም የደን ጭፍጨፋን የሚታደግ እና የግንባታ ዘርፉን ተወዳዳሪነት የሚጨምር እንደሆነ ማመላከታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.