ጨፌ ኦሮሚያ 8ኛ መደበኛ ጉባዔውን ከነገ ጀምሮ ያካሂዳል
አዲስ አበባ፣ የካቲት 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ጨፌ ኦሮሚያ 4ኛ ዓመት 6ኛ የስራ ዘመን 8ኛ መደበኛ ጉባዔውን ከነገ ጀምሮ እንደሚያካሂድ የጨፌው አፈ ጉባዔ ሰዓዳ አብዱራህማን ገለፁ።
በጉባዔው የ2017 በጀት ዓመት የስድስት ወራት የስራ አፈፃፀም ሪፖርት ቀርቦ የሚገመገም ሲሆን÷የቀሪው ስድስት ወራት እቅድ ሪፖርት የሚደመጥ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ሰላምና ፀጥታ፣ የልማት ስራዎች፣ መልካም አስተዳደርና አገልግሎት አሰጣጥ ከጨፌው አጀንዳዎች መካከል መሆናቸውን አንስተዋል።
የተስተዋሉ ክፍተቶችን በመገምገም ከማህበረሰቡ የተነሱ ጥያቄዎች እንዲሁም አስተያየቶች በጨፌው አባላት የሚቀርቡበት ጉባዔም ይሆናልም ነው ያሉት፡፡
በጉባዔው የተለያዩ ሹመቶች ቀርበው በአባላቱ ውይይት ከተደረገበት በኋላ ይፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በተያያዘም የጨፌውን የሥራ ሂደት ለማሳለጥ የሚረዳና መረጃዎችን በፍጥነት ለመለዋወጥ የሚያግዝ የጨፌ ኦሮሚያ የሞባይል መተግበሪያም ይፋ ተደርጓል።
መተግበሪያው ከኔዘርላንድስ መድበለ ፓርቲ ኢንስቲትዩት በተገኘ ድጋፍ የተዘጋጀ ሲሆን ፥ ስለ ጨፌው ማንኛውም ሰው መረጃን ሲፈልግ በዝርዝር የሚያገኝበት ነው ተብሏል።
በአፋን ኦሮሞ፣ በአማርኛና በእንግሊዘኛ ቋንቋዎች የሚሰራው መተግበሪያ ከዛሬ ጀምሮ በስራ ላይ እንደሚውል ተጠቁሟል።
በታምራት ደለሊ