Fana: At a Speed of Life!

አይኤምኤፍ ለኢኮኖሚ ሪፎርም ፕሮግራማችን የሚያደርገውን የቀጠለ ድጋፍ ዋጋ እንሰጠዋለን – ጠ/ሚ ዐቢይ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ የካቲት 1፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) አይኤምኤፍ ለኢኮኖሚ ሪፎርም ፕሮግራማችን የሚያደርገውን የቀጠለ ድጋፍ ዋጋ እንሰጠዋለን ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ፥ የዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋም (አይኤም ኤፍ) ማኔጂንግ ዳይሬክተር ክርስታሊና ጂኦርጂዬቫ በኢትዮዽያ ለሚያደርጉት ጉብኝት እንኳን ደህና መጡ ብለዋቸዋል፡፡

አይኤምኤፍ ለኢኮኖሚ ሪፎርም ፕሮግራማችን የሚያደርገውን የቀጠለ የቴክኒክ እና የገንዘብ ድጋፍ የእርስዎንም የግል ጥረት እና አስተዋፅዖ ከፍ ያለ ዋጋ እንሰጠዋለን ሲሉም ጠቅሰዋል።

በአይኤምኤፍ የገንዘብ ድጋፍ ከሚደረግላቸው ታላላቅ የድጋፍ መርሐ-ግብሮች አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ፕሮግራም በሀገር በቀል ርዕይ እና የለውጥ አጀንዳ ላይ የተመሠረተ የእድገት እና የልማት ህልሞቻችንን በሚገባ ቀርፆ የያዘ መሆኑም ተነስቷል፡፡

በዚህም ለረጅም ጊዜ የቆዩ የማክሮኢኮኖሚ ፈተናዎችን ለመሻገር የለውጥ ሥራዎቻችንን በጠንካራ ትኩረት እና ባለቤትነት በመያዝ ቆራጥ፣ ሁሉን አቀፍ እና ታሪካዊ ርምጃዎችን ወስደናል ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል።

በፕሮግራሙ እስካሁን የታዩ ውጤቶችም ቀና እና አበረታች ስለመሆናቸውም ጠቁመዋል፡፡

እየተካሄዱ ያሉ የትግበራ ሥራዎችም የማክሮኢኮኖሚ መረጋጋት፣ እድገትን ማፍጠን፣ የዜጎች ኑሮ ደረጃን ማሻሻል ሲሆኑ ፥ በዚህም ኢትዮጵያ የአፍሪካ የብልፅግና ተምሳሌት እንድትሆን ማስቻል እንደሆነም አጋርተዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.