የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች መገጣጠሚያ ፋብሪካ ተመረቀ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 2፣ (ኤፍ ኤም ሲ) ሶላሪስ ሞተርስ የተሰኘ በኤሌክትሪክ የሚንቀሳቀሱ ባለ 2 እና 3 እግር ተሽከርካሪዎች መገጣጠሚያ ፋብሪካ ዛሬ ተመርቋል፡፡
በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ጎልባ ቀበሌ የተገነባው ፋብሪካው በክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አብዱ ሁሴን(ዶ/ር) ተመርቆ ተከፍቷል፡፡
የድርጅቱ ስራ ስኪያጅ ወ/ሮ ቃልኪዳን ንጉሴ÷ፋብሪካው በ400 ሚሊየን ብር ካፒታል ወደ ስራ መግባቱን ገልፀው አሁን ላይ በሙከራ ምርት የ280 ተሸከርካሪዎችን መገጣጠም መቻሉን ተናግረዋል።
ተሽከርካሪዎቹ ሰባት ሰው የመያዝ አቅም ያላቸውና በአንድ ጊዜ ቻርጅ 150 ኪሎ ሜትር የሚጓዙ በመሆናቸው አሁን ላይ ካሉት ተመሳሳይ ባለሶስት እግር ተሽከርካሪዎች ተመራጭና አዋጭ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል ነው ያሉት ።
ፋብሪካው በቀን 30 ተሽከርካሪዎችን የመገጣጠም አቅም አለው ያሉት ስራ አስኪያጇ÷ በተመሳሳይ በቀን 30 የነዳጅ ባለ 3 እግር ተሽከርካሪዎችን ወደ ኤሌክትሪክ የመቀየር አቅም እዳለውም ተናግረዋል ።
በቀጣይ ባትሪ ብቻ በማስመጣት ሌላውን የመኪና አካል እዚሁ አምርቶ የመገጣጠም ስራ ይሰራልም ነው ያሉት ፡፡
በአበበ የሸዋልዑል