Fana: At a Speed of Life!

ጉባኤዎቹ በስኬት እንዲጠናቀቁ በቂ ዝግጅት ማድረጉን ጥምር ኃይሉ አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 3፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) 38ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ እና 46ኛው የስራ አስፈፃሚ ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ በስኬት እንዲጠናቀቅ የፀጥታና ደኅንነት ጥምር ኃይል በቂ ዝግጅት አድርጎ ወደ ሥራ መግባቱን አስታውቋል።

የፀጥታና ደኅንነት ጥምር ኃይል እስከአሁን ድረስ በአዲስ አበባና በሀገር ዓቀፍ ደረጃ የተከናወኑ የፀጥታ ስራዎች ስኬታማ መሆናቸውን ገምግሟል፡፡

38ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ እና 46ኛው የስራ አስፈፃሚ ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ በስኬት እንዲጠናቀቅ አዳዲስ ሎጅስቲክ አቅሞችን በመጠቀም ከፍተኛ ቁጥር ያለው የፀጥታ ኃይል በማሰማራት በቴክኖሎጂ የታገዘ የፀጥታና የደኅንነት ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጿል።

በተከታታይ እየተካሄደ ያለው የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ፣ ብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት፣ የሪፐብሊካን ጋርድ፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ እና ሌሎች አጋር የፀጥታ አካላት የተቀናጀ ኦፕሬሽን አዲስ አበባ ከተማ ፍፁም ሰላማዊ ሆና እንድትቀጥል ያስቻለና አሁን ላይ የከተማዋ ሰላም በአስተማማኝ ሁኔታ መቀጠሉን በግምገማው ያረጋገጠ መሆኑን ያመላከተው የፀጥታና ደኅንነት ጥምር ኃይል ባካሄደው ግምገማ ለተገኘው ሰላም እና በተካሄደው ኦፕሬሽን ለተገኘው ውጤት የህዝቡ ተሳትፎ ከፍተኛ ነበረ ብሏል።

አዲስ አበባ ከተማ የአፍሪካ ሕብረት እና የተለያዩ የዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ በመሆኗ ፀጥታዋ ፍጹም ሰላማዊ ሆኖ እንዲቀጥልም ከመቼውም ጊዜ በላይ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት እየሰራ እንደሚገኝ በግምግማው ተነስቷል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ እንደ ሀገር ሁሉም የፀጥታ መዋቅር የሚመለከተውን የሥራ ድርሻ ወስዶ አካባቢውን ፍፁም ሰላማዊ ለማድረግ በኃላፊነትና በተጠያቂነት የድርሻውን እየተወጣ እንደሚገኝ ገልጿል።

በጉባኤው ላይ የሚታደሙ እንግዶችን በኢትዮጵያዊ ወግና ባህል በመቀበል እና በማስተናገድ በቆይታቸዉ ጊዜ በተለያዩ አካባቢዎች ሲንቀሳቀሱ፤ ካረፉባቸው ሆቴሎች ወደ መሰብሰቢያ አዳራሽ በሚሄዱበት ወቅት ሰላም ወዳዱ ሕዝብ በባለቤትነት የሚጠበቅበትን የዜግነት ድርሻውን በኃላፊነት እንዲወጣና ለፀጥታ አካላት እያደረገ ያለውን ቀና ትብብርም አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥምር ኃይል ጥሪ አቅርቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.