ግዳጁን በምንም ሳይገደብ በላቀ ደረጃ መፈፀም የሚችል የልዩ ሃይል ፀረ-ሽብር ተገንብቷል – ሌ/ጄ ሹማ አብደታ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 3፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ማንኛውንም ግዳጅ በየትኛውም ቦታ እና የአየር ፀባይ መፈፀም የሚችል የልዩ ሃይል ፀረ-ሽብር መገንባቱን የኮማንዶና አየር ወለድ ዕዝ አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ሹማ አብደታ ገለፁ፡፡
ሌ/ጄ ሹማ አብደታ ስልጠናቸውን ያገባደዱ የልዩ ሃይል አባላትን በማነጋገር ስታር ዊንግ ደረጃ ለደረሱት የአየር ወለድ አሰልጣኞች በለኮከብ ክንፍ አልብሰዋል፡፡
በዚህ ወቅትም ልዩና ውስብስብ ስልጠና ወስደው የተዘጋጁት የልዩ ሃይል ፀረ-ሽብር አባላት የሀገሪቷ የመጨረሻ ሃይል በመሆናቸው ብዙ እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል፡፡
ይሄን በመገንዘብም በግልም ሆነ በቡድን የትኛውንም ፈተና በማለፍ የሚሰጣቸውን ሀገራዊ ተልዕኮ ለመፈፀም መዘጋጀት እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡
ከጠላት ጀርባ ግራና ቀኝ ከአየር በመውረድ የጠላትን ስበት ማዕከል በመደምሰስ ሌላኛውን የሠራዊት ክፍል ለድል ማብቃት እንዲሁም በሀገር ውስጥ ይሁን ከሀገር ውጭ ህዝብንና ሀገርን የሚያሸብር ማስተር ማይንድ መምታት ከዚህ ክፍል ግዳጆች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው ብለዋል፡፡
ሌተናል ጄኔራል ሹማ ከፍሉም ይህንን አቅም በላቀ ደረጃ እንዲኖረው ተደርጎ መገንባቱን ነው ያብራሩት፡፡