በአቶ አደም ፋራህ የተመራ ልዑክ በዓለም የመንግስታት ጉባዔ ላይ እየተሳተፈ ነው
አዲስ አበባ፣ የካቲት 4፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በም/ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ሃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ም/ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ የተመራ ልዑክ በዱባይ እየተካሄደ በሚገኘው የዓለም የመንግስታት ጉባዔ ላይ እየተሳተፈ ነው።
በአቶ አደም ፋራህ የተመራ ከፍተኛ የኢፌዲሪ ልዑካን ቡድን የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች ዱባይ ገብቷል፡፡
ልዑካኑ ዱባይ ዓለም ዓቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች፣ በተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች የኢትዮጵያ አምባሳደር ዑመር ሁሴን (ዶ/ር) እና ዲፕሎማቶች አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡
ልዑካኑ በዱባይ ቆይታቸው በከተማዋ እየተካሄደ በሚገኘው የዓለም የመንግስታት ጉባዔ ላይ እየተሳተፉ መሆኑን የፓርቲው መረጃ ያመላክታል፡፡
የልዑካን ቡድኑ አባላት በጉባዔው በከፍተኛ ደረጃ የሁለትዮሽና ባለብዙ ወገን መድረኮች፣ በፓናል ውይይቶች እንዲሁም በጎንዮሽ መስተጋብራዊ ክፍለ ጊዜዎች ላይ ተሳትፎ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን፣ ውጤታማ ፖሊሲ መቅረጽ፣ የዜጎች ተሳትፎ፣ ዘላቂ ልማት፣ የውሃና መስኖ አጠቃቀምና የሕዝብ አገልግሎት አሰጣጥ የመድረኩ ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫዎች መሆናቸው ተገልጿል፡፡
በመርሐ- ግብሩ መክፈቻ ላይ መንግስታዊ የአስተዳደር አቅምን በሚያዳብሩ ዓለም አቀፋዊ ስጋቶች እና እድሎች ላይ ምክክር መደረጉ ተጠቁሟል፡፡