Fana: At a Speed of Life!

በጋምቤላ ከተማ የኮሪደር ልማት ሥራ ተጀመረ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 4፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አለሚቱ ኡሞድ በጋምቤላ ከተማ 14 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የአራት መንገዶች የኮሪደር ልማት ሥራ አስጀምረዋል።

መንገዶቹ ከአቦቦ ኬላ እስከ ባሮ ድልድይ፣ ከባሮ ድልድይ እስከ ዶንቦስኮ፣ ከአደባባይ እስከ ዲፖ እና ከአደባባይ እስከ ቄራ ያሉት መሆናቸው ተጠቁሟል።

የኮሪደር ልማት ሥራው የአረንጓዴ ልማት፣ የእግረኛ መንገድ፣ የማረፊያ ስፍራዎች፣ የብስክሌት መንገድ እና የማስ ስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን ያካተተ ነው ተብሏል፡፡

በኮሪደር ልማቱ የሚለሙት መንገዶቹ ለተለያዩ የመሠረተ ልማት ሥራዎች አመቺ እንዲሆኑ እስከ 36 ሜትር ስፋት እንደሚኖራቸው ተጠቁሟል፡፡

ወ/ሮ አለሚቱ ኡሞድ በዚህ ወቅት÷ፕሮጀክቱ የጋምቤላ ከተማን ደረጃ በማሻሻል ለኑሮ እና ለኢንቨስትመንት ተመራጭ ለማድረግ ያስችላል ብለዋል፡፡

ህብረተሰቡ በልማት ዙሪያ የሚያደርገውን ቀና ትብብር እንዲያጠናክርም ርዕሰ መስተዳድሯ ጥሪ አቅርበዋል።

የኮሪደር ልማት ስራው ከ1 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የሚከናወን መሆኑን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ አመላክቷል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.