Fana: At a Speed of Life!

የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔን በተሳካ ሁኔታ ለማስተናገድ ሁለንተናዊ ዝግጅት ተደርጓል- አገልግሎቱ

 

አዲስ አበባ፣ የካቲት 4፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) 38ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔን በተሳካ ሁኔታ ለማስተናገድ ሁለንተናዊ ዝግጅት መደረጉን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ፡፡

አገልግሎቱ የተደረገውን ዝግጅት አስመልክቶ ያወጣው ወቅታዊ መግለጫ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

ወቅታዊ መግለጫ

 

ሃገራችን ኢትዮጵያ በያዝነው ሳምንት መጨረሻ የሚካሄደውን የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔ ከወትሮው በላቀ መልኩ በድምቀት ለማስተናገድ አስፈላጊውን ሁሉ ቅድመ ዝግጅት በማጠናቀቅ እንግዶቿን ለመቀበል ዝግጁ ሆናለች።

 

ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ኅብረት ምስረታም ሆነ ከተመሰረተ በኋላ ከሌሎች የአፍሪካ ሃገራት ጋር በመሆን ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጋለች። የኅብረቱ መቀመጫ እንደመሆናችንም በየዓመቱ የሚካሄዱ የአስፈጻሚዎች እና የመሪዎች ስብሰባዎችን በድምቀት ስናስተናግድ ቆይተናል።

 

የአፍሪካ ኅብረት ሃገራችን ኢትዮጵያ ለፓን አፍሪካኒዝም ማቆጥቆጥና መለምለም የተወጣችውን ሚና የሚዘክር ቋሚ ሃውልታችን ነው።

 

ከዚህም ባሻገር ሌሎች አፍሪካውያን ወንድም እህቶቻችን ለሃገራችን ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ስኬት የዋሉትን ውለታ የሚዘክርና በተለይም በተቸገርንባቸው ጊዜያት ሁሉ አፍሪካውያን ወገኖቻችን ያደረጉልንን ድጋፍና አለሁ-ባይነት የሚያሳይ ነው። ኢትዮጵያ የአፍሪካ ማዕከል እንድትሆን ከሚያደርጓት በርካታ ምክንያቶች አንዱ የአፍሪካ ኅብረት እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶች መቀመጫ መሆኗ ነው።

 

በያዝነው ሳምንት ለ46ኛ ጊዜ የሚካሄደው የአስፈጻሚዎች መደበኛ ስብሰባ እና ለ38ኛ ጊዜ የሚከናወነው የመሪዎች ጉባዔ ከወትሮው በላቀ መልኩ በርካታ እንግዶች የሚገኙበት ነው።

 

በጉባዔው ከ15ሺህ በላይ እንግዶች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል። ይህንን ኹነት በተሳካ ሁኔታ ለማከናወን የተቋማትን ቅንጅትና መናበብ በሚያረጋግጥ መልኩ 35 የፌደራል ተቋማት እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳድር ያሉበት ዐብይ ኮሚቴ እና ንዑሳን ኮሚቴዎች ተቋቁመው በየጊዜው በመገምገግም ስራውን በውጤታማነት መርተዋል።

 

እንግዶቻችን በሚኖራቸው ቆይታ ከስብሰባውም በተጨማሪ በሃገራችን ያሉ የቱሪስት መዳረሻዎችን እንዲጎበኙ፣ የልማት ጥረቶችንና ውጤቶችን ተዟዙረው እንዲያዩ፣ የኢትዮጵያን ምርቶች እንዲቋደሱና እንዲገበያዩ ለማድረግ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ ይጠይቃል። ለዚህም እንግዶችን ተቀብለን በምናስተናግድበት ወቅት እንደ ሙያ ዘርፋችን ብቻ ሳይሆን እንደ አንድ እንግዳ ተቀባይ ኢትዮጵያዊ መሆን አለበት።

 

እስከ ጉባዔው ፍጻሜ ድረስ በሚኖሩት ቀናት ከመንገድ መዘጋጋት ጋር ተያይዞ የሚኖሩ መጠነኛ መስተጓጎሎችን ሃገራችን ይህን ከፍተኛ ትርጉም ያለው አህጉራዊ ኹነት በማስተናገዷ ከምናገኘው ጥቅም አንጻር በማየት በተለመደው እንግዳ ተቀባይነታችን እንድናስተናግድ ጥሪውን ያቀርባል።

 

የቀን ውሏችንን ከመርሃ ግብሩ ጋር ለማሰናኘት ከወዲሁ አስፈላጊውን ዝግጅት እንድታደርጉ እያሳሰብን፣ ለዚህም ይረዳ ዘንድ በሚመለከታቸው የመንግስት አካላት የሚሰጡ መረጃዎችን በቅርበት እንድትከታተሉ ማሳሰብ እንወዳለን።

 

በመጨረሻም ይህ ቅድመ ዝግጅት በተሳካ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ ሌት ተቀን ለሰሩ የፌደራል እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳድር ተቋማት የመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት የላቀ ምስጋናውን ያቀርባል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.