ህዝብን ለምሬት የሚዳርጉ ብልሹ አሰራሮችን መቅረፍ ይገባል- አቶ ሙስጠፌ መሃመድ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 4፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ህዝብን ለምሬት የሚዳርጉ ብልሹ አሰራሮችን መቅረፍ እንደሚገባ የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሃመድ ገለፁ።
የሶማሌ ክልል ከፍተኛ አመራሮች በሁለተኛው የብልፅግና ፓርቲ መደበኛ ጉባኤ ውሳኔዎችና የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ውይይት አካሂደዋል።
በውይይቱ ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ÷ አመራሩ የውስጠ ዴሞክራሲ ስርዓትን በማጎልበት ጠንካራ ሀገረ መንግስት ለመገንባት በሚደረገው ጥረት የበኩሉን ሚና በላቀ ተነሳሽነት መፈፀም እንደሚገባው ገልጸዋል።
የአገልግሎት አሰጣጥ ስርዓትን በማዘመንና በቴክኖሎጂ በመደገፍ ህዝብን ለምሬት የሚዳርጉ ብልሹ አሰራሮችን መቅረፍ ይገባል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ በክልሉ በፐብሊክ ሰርቪስ ዘርፍ የተጀመሩ ሪፎርሞች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ሲሉ ተናግረዋል።
በክልሉ በግብርና፣ በአምራች ኢንዱስትሪ፣ በከተማ ልማት እና በሌሎች መስኮች የተገኙ ድሎችን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር አመራሩ በትኩረት ሊሰራ ይገባልም ብለዋል።
አመራሩ በፓርቲው የተቀመጡ አቅጣጫዎች በተሟላ መንገድ ገቢራዊ መሆናቸውን በመከታተል እና የሚያጋጥሙ ችግሮችን በመፍታት ሀላፊነቱን በብቃት እንዲወጣም መመሪያ መስጠታቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን የተገኘው መረጃ ያመላክታል።