Fana: At a Speed of Life!

አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣናን እውን ለማድረግ ያለቪዛ ጉዞን መተግበር እንደሚገባ ተመላከተ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 5፣ 2017(ኤፍ ኤም ሲ) ከቪዛ-ነጻ እንቅስቃሴ ለአፍሪካ ትራንስፎርሜሽን በሚል ርዕሰ ጉዳይ ላይ ያተኮረ የሚኒስትሮች ስትራቴጂካዊ ውይይት ተካሂዷል፡፡

በመድረኩ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌን (ዶ/ር) ጨምሮ ከአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ የተለያዩ ባለድርሻ ሀገራት ተሳትፈዋል፡፡

አፍሪካውያን ያለቪዛ ከአንድ ሀገር ወደሌላኛው የአፍሪካ ሀገር መጓዝ የሚችሉባቸው አመቺ ሁኔታዎችና ተግዳሮቶች በመድረኩ ተነስተዋል።

በአፍሪካ ሰዎች በነፃነት እንዲንቀሳቀሱ ለማድረግ የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ ሲሆን÷እንቅስቃሴውን እውን ለማድረግ ርምጃ ከወሰዱ ሀገራት መካከል ርዋንዳ፣ጋና፣ጋሚቢያ፣ ቤኒና ሲሼልስ ይጠቀሳሉ።

አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣናን እውን ለማድረግ ያለቪዛ ጉዞን ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን÷ከቪዛ ነፃ አፍሪካን መፍጠር የአፍሪካውያን የእርስ በርስ ግንኙነትን ለማጠናከር እንደሚያግዝ ተጠቁሟል።

በዚሁ ወቅት ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር)÷ኢትዮጵያ ቀጣናዊና አህጉራዊ ትስስሮችና ከማጠናከር ረገድ የዳበረ ቁርጠኝነትና የመሪነት ሚና ያላት ሀገር ናት ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ለአፍሪካዊያን የነፃነት ቀንዲል የሆነች፣በራስ ለመተማመን ስነልቦና መሰረት የጣሉ ድሎችን ያስመዘገበች፣ ከአፍሪካውያን አልፋ ለመላው ጥቁር ሕዝቦች የይቻላል መንፈስን ያሰረጸች ሀገር ናት ሲሉም አውስተዋል፡፡

በቅድስት አባተ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.