Fana: At a Speed of Life!

ዓለም አቀፍ ፈተናዎችን ለመቋቋም አፍሪካዊ አንድነትን ማጠናከር አለብን – ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ የካቲት 5፣ 2017(ኤፍ ኤም ሲ) እያጋጠሙ ያሉ ዘርፈ ብዙ ዓለም አቀፍ ፈተናዎችን ለመቋቋም አፍሪካዊ አንድነትን አጠናክረን መቀጠል አለብን ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴቲስ (ዶ/ር) ተናገሩ።

በ46ኛው የአፍሪካ ሕብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብስባ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ÷ በአሁኑ ወቅት የባለብዙ ወገን የግንኙነት መስክ ከባድ ፈተና እያጋጠመው መሆኑን ገልጸዋል።

ለአፍሪካ የባለብዙ ወገን ግንኙነት ተመራጭ እና አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመው÷ይህ የግንኙነት ዘርፍ ምርጫችን ሊሆን የሚገባው በትብብር፣ በጋራ መግባባት እና በአጋርነት ስለምናምን ነው ብለዋል።

አሁን ላይ እያጋጠሙ ያሉ ፈተናዎች አብዛኛዎቹ ዓለም አቀፍ በመሆናቸው መፍትሔዎቻቸውም ዓለም አቀፍ እና የባለብዙ ወገን ግንኙነት ማዕቀፍን የሚሹ መሆናቸውን አንስተዋል።

የአየር ንብረት ለውጥ፣ የአካባቢ ብክለት፣ የበርሃማነት መስፋፋት፣ ወረርሽኝ እና መሰል ዓለም አቀፍ የጤና ጉዳዮች የባለብዙ ወገን የትብብር ማዕቀፍን የሚጠይቁ ናቸው ብለዋል ሚኒስትሩ።

እነዚህን ችግሮች ለመፍታት የተባበሩት መንግሥታት፣ የአፍሪካ ሕብረት እና መሰል የባለብዙ ወገን መድረኮችን እና ተቋማትን ለማጠናከር የሚደረገው ጥረት መጨመረ እንዳለበትም አስረድተዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ የቴክኖሎጂ ለውጦች እና የጂኦ ፖለቲካዊ ፉክክሮች እያየሉ ምጣታቸውን ጠቅሰው÷ አፍሪካዊ አንድነት ከመቼውም ጊዜ በላይ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።

እንደ አህጉር የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤትን ጨምሮ በሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶች ማሻሻያ እንዲደረግባቸው መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል።

ኢትዮጵያ ለአህጉሩ ኢኮኖሚ ተስፋ ሰጭ በሆነው አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና የንግድ ሥራ ለመጀመር ቁርጠኛ መሆኗን አስገንዝበዋል፡፡

የአፍሪካ ሕብረት የቡድን 20 አባል መሆኑ በዓለም አቀፍ መድረክ አህጉራዊ ጥቅሞችን ለማስከበር ዕድል እንደሚፈጥር ኢትዮጵያ ታምናለች ብለዋል።

በለይኩን ዓለም

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.