ጌዲዮን ጢሞቲዎስ(ዶ/ር) ከሞሮኮ እና ቱኒዚያ አቻቸው ጋር መከሩ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 5፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ(ዶ/ር) ከሞሮኮ ውጭ ጉዳይ እና አፍሪካ ትብብር ሚኒስትር ናስር ቦሪታ እና ከቱኒዚያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሞሀመድ አሊ ናፍቲ ጋር ተወያይተዋል፡፡
ሚኒስትሩ በዛሬው እለት ከተጀመረው 46ኛው የአፍሪካ ሕብረት መደበኛ የአስፈጻሚ ምክር ቤት ስብሰባ ጎን ለጎን ነው ከሞሮኮ እና ቱኒዚያ አቻዎቻቸው ጋር የተወያዩት፡፡
ሚኒስትሩ ከሞሮኮው አቻቸው ጋር ባደረጉት ውይይት አሁን ላይ ያለውን የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት የበለጠ በማሳደግ በንግድ ፣ ኢንቨስትመንት፣ ቱሪዝም ፣ ኢነርጂ፣አይሲቲ እና ትምህርት መስኮች በትብብር መሥራት በሚቻልባቸው መስኮች ዙሪያ መክረዋል።
የጋራ የሚነስትሮች ስብሰባን በቅርቡ ለማካሄድና በአህጉሪቱ ሰላም እና ጸጥታ ጉዳዮች በጋራ ለመስራትም ተስማምተዋል።
በተመሳሳይ ከቱኒዚያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር በነበራቸው ውይይት ÷ ታሪካዊውን የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት የበለጠ ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ተስማምተዋል፡፡
በተጨማሪም የሀገራቱን ግንኙነት ለማጠናከር የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ ማድረግ እንደሚገባ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡