Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ በምክር ቤት አባልነቷ ለአፍሪካ ሰላም መረጋገጥ ያላትን ሚና አጠናክራ እንደምትቀጥል ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 5፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በሰላም እና ደህንነት ምክር ቤት አባልነቷ ለአህጉሪቱ ሰላም መረጋገጥ ያላትን ሚና አጠናክራ እንደምትቀጥል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው ገለጹ።

46ኛው የአፍሪካ ሕብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብስባ “የማካካሻ ፍትሕ ለአፍሪካውያንና ዘርዓ-አፍሪካውያን” በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ ነው።

ከስብሰባው አጀንዳዎች መካከል የአፍሪካ ህብረት የሰላም እና ደህንነት ምክር ቤት የአምስት አባላት ምርጫ ይገኝበታል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው ኢትዮጵያ የሰላም እና ደህንነት ምክር ቤት አባል ሆና በከፍተኛ ድምጽ መመረጧን ገልጸዋል።

በተለይ በሰላም እና ጸጥታ በአካባቢዋ ብሎም በአህጉር ደረጃ እንደ አጀንዳ ይዛ የምትንቀሳቀስ ሀገር መሆኗን ጠቁመው ለዚህም ስኬት በቋሚነት ከምታደርገው አስተዋጽኦ እውቅና ከመስጠት የተነሳ ለአባልነት መመረጧን አስረድተዋል።

የአፍሪካ ህብረት በአጀንዳ 2063 ከሚሻቸው ትልሞች አንዱ ሰላምና ጸጥታ የሰፈነበት አህጉር ማየት መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በየጊዜው በተለይም በቀጣናው የራሷን ሰላም አስከባሪ በተለያዩ ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች በመላክ አስተዋጽኦ ስታደርግ መቆየቷን ገልጸው አባል ሆና መመረጧ የነዚህ ድምር ውጤት መሆኑን ጠቁመዋል።

በቆይታዋም ይህንኑ አጀንዳ ከሌሎች የአፍሪካ ህብረት አባል አገራት ጋር በመሆን የበለጠ የምታስፈጽም እና አተኩራ የምትሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የአፍሪካ ሰላም እና ጸጥታ ምክር ቤት የሚመክርባቸው አጀንዳዎች በተለያዩ አካባቢዎች የሚነሱ ግጭቶች ዘላቂ ሰላም እና መፍትሄ በሚያገኙበት ጉዳይ ላይ መምከር እና የመፍትሄ አቅጣጫ መስጠት መሆኑን ጠቁመዋል።

በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የአህጉሪቷ አካባቢዎች ግጭቶች መኖራቸውን ጠቅሰው፥እነኝህን ግጭቶች ከአባል አገራት ጋር በጋራ በመሆን ዘላቂ ሰላም ማምጣት የሚቻልበት መንገድ በቀጣይ የሚሰራበት አጀንዳ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያም ያላትን አቅም ከሌሎች አገራት ጋር በመሆን እንደምትሰራ ማስረዳታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.