ዳንጎቴ ግሩፕ በኢትዮጵያ ተጨማሪ የኢንቨስትመንት ዘርፍ እንደሚሰማራ አስታወቀ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 8፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአፍሪካ ግንባር ቀደም የሆነው ዳንጎቴ ግሩፕ በኢትዮጵያ በተጨማሪ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ እንደሚሰማራ አስታወቀ።
በአፍሪካ ግንባር ቀደም የሆነው ዳንጎቴ ግሩፕ ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ጋር በዛሬው እለት በሰጠው መግለጫ በኢትዮጵያ እያከናወናቸው ስላሉት የማስፋፊያ ስራዎች ማብራሪያ ሰጥቷል።
የዳንጎቴ ግሩፕ ሊቀ መንበርና ዋና ስራ አስፈፃሚ አሊኮ ዳንጎቴ፣ ኢትዮጵያ ለባለሀብቶች የሰጠችው ትኩረት አስደናቂ እንደሆነ ገልፀው በኢትዮጵያ እያደረጉት ባለው የኢንቨስትመንት ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ስራ አስፈፃሚው፣ ኩባንያው በኢትዮጵያ በቀጣይ በስኳር ኢንዱስትሪ እንዲሁም እንደ ማዳበሪያ ባሉ የግብርና ግብዓቶች ማምረት ተግባር ላይ እንደሚሰማሩ ገልፀዋል።
አፍሪካ የምትለማው በአፍሪካውያን ነው ያሉት አሊኮ ዳንጎቴ፣ የፖለቲካ መሪዎቻችን የአፍሪካ ህብረትን ለማጠናከር በሚሰሩበት ወቅት እኛ የንግድ መሪዎች እንደመሆናችን መጠን በአህጉሪቱ ያለውን የንግድ ትስስራችንን በማጠናከር ጥረቱን መደገፍን አለብን ብለዋል::
በሰማኸኝ ንጋቱ