አፍሪካውያንና የተሻለ ነገ ለመገንባት በአንድነት ሊቆሙ ይገባል- የባርባዶስ ጠቅላይ ሚኒስትር
አዲስ አበባ፣ የካቲት 8፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ)የባርባዶስ ጠቅላይ ሚኒስትር ሚያ አሞር ሞትሌይ አፍሪካውያን የተሻለ ነገ ለመገንባት በአንድነት እንዲቆሙ ጥሪ አቀረቡ።
በ38ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትሯ፤ የዓድዋ ድል መንፈስ ታጥቄ ከፊታችሁ ቁሚያለሁ ብለዋል።
የዓድዋ ድል እብሪተኛ ወራሪዎች ድል የነሳ እና ለመላው ጥቁሮች የነጻነት መንፈስ ያወረሰ መሆኑን ጠቅሰው፤ በዓድዋ ድልና በፓን አፍሪካዊነት እሳቤ ውህደትን ማፋጠን ይገባናል ነው ያሉት።
የካሪቢያን ማህበረሰብ ከአፍሪካውያን ወንድም እህቶቻቸው ጋር አንድነታቸውን የማጠናከር ጽኑ ህልማቸውን ጠቅሰዋል።
የካረቢያን ማህበረሰብ በዓለም ላይ አንደኛና ሁለተኛ ዜጋ ሊኖር አይገባም በሚል ኢ-ፍትሃዊነትና ግፍን በመታገል የተጫወቱትን ሚና አውስተዋል።
አፍሪካውያን በቅኝ ግዛት፣ በባሪያ ንግድና በሌሎች መዋቅራዊ በደሎች የማካካሻ ፍትሕ እንደሚሹ መጠቀሳቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በዚህ ዘመንም አይነተ ብዙ በደሎች እንዳሉ የኮቪድ ወረርሽኝ ወቅት መድሎዎች፣ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ እና የቅኝ ግዛት ወለድ ያላባሩ ግጭቶችን ለአብነት አንስተዋል።
መሰል በደሎችና አግላይ ስርዓቶች እንዳይቀጥሉ በአንድነት ቆመን መታገል አለብን፤ ዕድሉ በእጃችን ነው ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
አፍሪካውያንና ዘርዓ አፍሪካውያን የተሻለ ነገ ለመገንባት በተባበረ አቅም በአንድነት መቆም እና ከጥገኝነት መላቀቅ አለብን ብለዋል።
ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የማካካሻ ፍትሕ ጥያቄያችን ለአዲሱ የዓለም ትውልድ በደልን ሳይሆን ፍትሕን፣ ብልፅግናን እና የተረጋጋ ስርዓትን የማስረከብ ጉዳይ መሆኑን መገንዘብ አለበት ብለዋል።