Fana: At a Speed of Life!

ወደ ውጭ ከተላኩ ሥጋ እና የወተት ተዋጽኦዎች 72 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ገቢ ተገኘ

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 24 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ወደ ውጭ ከተላኩ ሥጋ እና የወተት ተዋጽኦዎች 72 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ገቢ መገኘቱን የኢትዮጵያ የሥጋ እና የወተት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡

የኢትዮጵያ ሥጋና ወተት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ኃይለስላሴ ወረስ ለኢዜአ እንደገለጹት አብዛኛው ገቢ ከበሬ፣ ፍየል እና የበግ ሥጋ ምርት ውጤቶች የተገኘ ነው፡፡

ቀሪው ገቢ ደግሞ ከሌሎች እንስሳትና የእንስሳት ተዋጽኦ መሆኑን ጠቁመው በዚህም ወተት፣ ማር፣ ሰም እና ዓሳ ወደ ውጭ መላካቸውን ተናግረዋል፡፡

እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ በሚያዚያ እና በግንቦት ወራት ከኢትዮጵያ ወደ ዱባይ እና ሳዑዲ ዓረቢያ የተላከ የዘርፉ ወጪ ንግድ ጭማሪ አሳይቷል፡፡

ከኢትዮጵያ ወደ ሃገራቱ የሚደረገው በረራ ከመቋረጡ በፊት በቀን የ100 ቶን የሥጋ ፍላጎት እንደነበር ያወሱት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ሃገራቱ ሥጋና የሥጋ ውጤቶችን ከኢትዮጵያ ለማስገባት ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

በኮሮናቫይረስ እና በእንስሳት እጥረት ሳቢያ የበረራ አገልግሎት መቋረጡ ከዘርፉ ለማግኘት የታቀደውን 124 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ገቢ ለማሳካት እንቅፋት መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.