ጎረቤት ሀገራትን ጭምር ታሳቢ ያደረገ የአደገኛ ኬሚካሎች ማስወገጃ ሊገነባ ነው
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 2፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ከራሷ አልፎ የጎረቤት ሀገራትን ጭምር ታሳቢ ያደረገ የአደገኛ ኬሚካሎች ማስወገጃ ልትገነባ መሆኑን የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ለሊሴ ነሜ (ኢ/ር) ገለጹ፡፡
ዋና ዳይሬክተሯ እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ በፈረመቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች መሰረት በሰውና በአካባቢ ላይ ጉዳት የሚያደርሱ አደገኛ ኬሚካሎች ወደ ሀገር እንዳይገቡ ቁጥጥር እያደረገች ነው።
የጤና ተቋማት፣ ትምህርት ቤቶች እና ሌሎች ድርጅቶች አስፈላጊ ኬሚካሎችን ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባት እንደሚችሉም ተናግረዋል።
ኬሚካሎቹ የአገልግሎት ጊዜያቸው ሲያልፍ በአግባቡ መወገድ እንዳለባቸው ገልጸው፤ ካልተወገዱ በሰው፣ ጤናና በአካባቢ ሥነ ምህዳር ላይ የከፋ ጉዳት የሚያደርሱ በመሆናቸው አስገንዝበዋል።
በመሆኑም የአገልግሎት ጊዜ ያለፈባቸውን ኬሚካሎች ያስገቡ ተቋማት እንዲያስወግዱ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አደገኛ ኬሚካሎች የት እና በምን ሁኔታ እንደሚገኙ ለማወቅ የዳሰሳ ጥናት መደረጉን ገልጸው፤ ጤና ሚኒስቴር የአገልግሎት ጊዜያቸው ያለፈባቸው መድኃኒቶችና ኬሚካሎችን የሚያስወግድበት ሥፍራዎችን ገንብቷል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም የአደገኛ ኬሚካሎች ማስወገጃ እንዳልነበራት ጠቅሰው፤ መንግሥት የጎረቤት ሀገራትን ጭምር ታሳቢ ያደረገ የኬሚካል ማስወገጃ ለመገንባት የዲዛይን ጥናት እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡