ታላቁ የጎዳና ላይ ኢፍጣርና የቁርዓን ውድድር በመጪው እሑድ ይካሄዳል
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 4፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ሀገር አቀፍ የቁርዓን ውድድር እና ታላቁ የጎዳና ላይ ኢፍጣር ሥነ-ሥርዓት በመጪው እሁድ መጋቢት 7 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ አስታውቋል፡፡
‘ቁርዓን – የእውቀትና የሰላም ምንጭ’ በሚል መሪ ሃሳብ ሀገር አቀፍ የቁርዓን ውድድሩ የማጣሪያ መድረክ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ም/ቤት ፕሬዚዳንት ጽ/ቤት ኃላፊ ኡስታዝ አቡበከር አሕመድ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ ቁርዓን በሁሉም መስክ የሰዎችን ሕይወት በቀና መንገድ በመምራት ለማህበረሰብ ከፍታ መሰረት መሆን የቻለ ነው።
በዚህ አግባብ ውድድሩ ይህን የቁርዓን ክብርና ከፍታ ለመግለጥ የተዘጋጀ መሆኑን ነው የተናገሩት።
ውድድሩ ቁርዓንን በልቦናቸው የተሸከሙ ሃፊዝ ወጣቶችን ለማበረታታትና ቀጣይ ተተኪ ትውልዶችን ለመፍጠር ያለመ ነው ብለዋል።
ዋናው ሀገር አቀፍ የቁርዓን ውድድር እሑድ መጋቢት 7 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ እንደሚካሄድ አመልክተዋል፡፡
በዚሁ ቀን በርካታ አማኞች የሚታደሙበት ታላቁ የጎዳና ላይ ኢፍጣር ሥነ ሥርዓት ‘ከኢፍጣር እስከ ቁርዓን’ በሚል መሪ ሀሳብ እንደሚከናወን ጠቁመው፤ ሕዝበ ሙስሊሙ በሁለቱ ታላላቅ መርሐ ግብሮች ላይ እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርበዋል።
በመራኦል ከድር