Fana: At a Speed of Life!

አቶ አደም ፋራህ ከኩባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 4፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ  ከኩባ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ብሩኖ ሮድሪጌዝ ፓሪላ ጋር ተወያይተዋል።

 

አቶ አደም በዚሁ ወቅት፡ ኢትዮጵያና ኩባ በደም የተሳሰረ ጠንካራ ግንኙነት እንዳላቸው ጠቅሰው፤ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸው ይበልጥ እንዲጠናከር ይሰራል ብለዋል።

 

ኩባ  በሰው  ሀብት አቅም ግንባታ  ዘርፍ  ከኢትዮጵያ ጋር ውጤታማ ግንኙነት እንዳላት ጠቅሰው 4 ሺህ ኢትዮጵያውያን በኩባ የትምህርት ዕድል ተጠቃሚ መሆናቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል።

 

በጤናው መስክም ኩባ ለኢትዮጵያ ትልቅ እገዛ እያደረገች መሆኗን ገልጸው ይሄው ትብብር ተጠናክሮ  ሊቀጥል እንደሚገባው አንስተዋል።

 

የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በሁሉም መስክ የሚለውጥ የሪፎርም ስራዎች ተግባራዊ እየተደረጉ መሆኑን ጠቅሰው በዚህም አመርቂ ውጤቶች እየተገኙ መሆኑን አብራርተዋል።

 

በግብርና በተለይም በስንዴ ምርት ራስን የመቻል ግብ መሳካቱን ገልጸው፤ በአምራች ኢንዱስትሪው፣ እንዲሁም በዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ላይ ሰፋፊ  ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም አስረድተዋል።

 

የኩባ  የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ብሩኖ ሮድሪጌዝ ፓሪላ በበኩላቸው፤ 50 ዓመታት ያስቆጠረውን የሀገራቱ ግንኙነት ሀገራቱ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር በላቀ ደረጃ መረባረብ ይገባል ብለዋል።

 

ኢትዮጵያ በቀጣናው ብሎም በአፍሪካ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን የምትጫወተውን ሚና ማድነቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

 

በኢኮኖሚ መስክ በንግድና ኢንቨስትመንት ሀገራቱ ግንኙነታቸውን ይበልጥ ማጎልበት እንደሚኖርባቸውም ነው ያመላከቱት።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.