Fana: At a Speed of Life!

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በ2012 በጀት ዓመት ለ15 ሺህ 563 መዛግብት እልባት መስጠቱን ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 2፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በ2012 በጀት ዓመት ለ15 ሺህ 563 መዛግብት እልባት መስጠቱን አስታወቀ።

የፍርድ ቤቱ ከፍተኛ አመራሮችና ዳኞች በዳኝነት ዘርፉ የ2012 ዕቅድ አፈጻጸም ላይ በዛሬው እለት ውይይት አካሂደዋል።

በውይይቱ ላይም የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በ2012 በጀት ዓመት ለ19 ሺህ 981 መዛግብት እልባት ለመስጠት ከያዘው ዕቅድ ውስጥ ለ15 ሺህ 563 መዛግብት እልባት መስጠቱ ተገልጿል።

ይህም በበጀት ዓመቱ ከቀረቡለት 18 ሺህ 928 መዛግብት አንጻር አፈጻጸሙ 82 ነጥብ 22 በመቶ መሆኑን እንደሚያሳይም የፍርድ ቤቱ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት መረጃ ያመለክታል።

የፌዴራል ፍርድ ቤቶች የኮረና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል በከፊል ዝግ ሆነው እንዲቆዩ እስከተወሰነበት መጋቢት ወር ድረስ ዕልባት ማግኘት ከሚገባቸው 13 ሺህ 987 መዛግብት ውስጥ 12 ሺህ 085 መዛግብት ዕልባት በማግኘታቸው ተጠቅሷል።

ከመጋቢት 2012 ዓ.ም ፍርድ ቤቶች በከፊል ዝግ ሆኖ እንዲቆይ መወሰኑን ተከትሎ እስከ በጀት ዓመቱ መጨረሻ ድረስ በቀጠሮ ላይ ከሚገኙ እንዲሁም አዲሰ እና እንደገና ከተከፈቱ 6 ሺህ 840 መዛግብት መካከል ለ3 ሺህ 478 መዘግብት እልባት መሰጠቱም ተነግሯል።

እልባት ከተሰጣቸው 15 ሺህ 563 መዛግብት መካከል 14 ሺህ 780 ጉዳዮች ወይም 95 በመቶ ያህሉ ከአንድ ወር እስከ አንድ ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ ውሳኔ ያገኙ መሆናቸውም ተመላክቷል።

የመዝገብ አፈጻጸሙ ፍርድ ቤቱ በኮረና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በከፊል ዝግ ሆኖ በቆየበት ጊዜ ጭምር የተመዘገበ በመሆኑ አበረታች ውጤት የታየበት እንደነበር የውይይቱ ተሳታፊዎቹ ገልጸዋል።

ከመዛግብት አፈጻጸም በተጨማሪ ፍርድ ቤቱ በዕቅድ ባስቀመጣቸው ግቦች ላይ በተለይም የዳኝነት ነጻነት፣ ገለልተኝነትና ተጠያቂነት መርሆች አፈጻጸምን ለማሻሻል፣ የዳኝነት ጥራትን ለማሳደግ፣ የዳኝነት አገልግሎት ቅልጥፍናን ለማጎልበት እንዲሁም
የዳኝነት አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል በተሰሩ ስራዎች ላይ ውይይት ተካሂዷል፡፡

የሶስቱ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች የሆኑት የፌዴራል ጠቅላይ፣ ከፍተኛ እና መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች በ2012 በጀት ዓመት እቅድ አፈጻጸማቸው ላይ ነሐሴ 21 ቀን 2012 ዓ.ም የጋራ ውይይት በማድረግ በቀጣይ ስራዎች ላይ አቅጣጫ እንዲሚያስቀምጡ ታውቋል።

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.