Fana: At a Speed of Life!

በደቡብ ክልል የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች 160 ሺህ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል ፈጥረዋል

አዲስ አበባ፣ ነሀሴ 4 ፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ)በደቡብ ክልል ወደ ተግባር የገቡ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች 160 ሺህ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል መፍጠራቸው ተገለጸ፡፡

የክልሉ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን እንደገለጸው÷ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች በልዩ ልዩ የስራ መስኮች ተሰማርተው የሚገኙ ከ2 ሺህ በላይ የሚሆኑ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች 159 ሺህ 562 ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድል ፈጥረዋል።

ፕሮጀክቶቹ በዋናነት የግብርና፣ ኢንዱስትሪና አገልግሎት ዘርፎች ሲሆኑ በህብረተሰቡ ዘንድ የእውቀት፣ የክህሎትና የቴክኖሎጂ ሽግግርን በማስረጽ ረገድ የሚጠበቅባቸውን እያበረከቱ መሆናቸውን ኮሚሽኑ አስታውቋል ።

በግንባታ ሂደት ላይ የሚገኙ አዳዲስ ፕሮጀክቶችም በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ተጠናቀው ባለሀብቱንም ሆነ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ እንዲያደርጉ በልዩ ትኩረት እየተሰራ ስለመሆኑም ተገልጿል።

በሌላ በኩል ኮሚሽኑ እየተገባደደ በሚገኘው በጀት አመት በገቡት ውል መሰረት ወደ ልማት ባልገቡ 75 ፕሮጀክቶች ላይ የተለያዩ እርምጃ ወስዷል ።

በአሁኑ ወቅትም ለማልማት ጥያቄ ካቀረቡ ባለሀብቶች መካከል አስፈላጊውን መስፈርት ላሟሉ 189 ፕሮጀክቶች 14 ሺህ 690 ሄክታር የገጠርና የከተማ መሬት ለአልሚዎቹ እንዲተላለፍ የክልሉ ካቢኔ ውሳኔ ማስተላለፉን ከክልሉ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.