Fana: At a Speed of Life!

የኮሮና ቫይረስን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣው አዋጅ አፈፃፀም ከፍተኛ ክፍተት እየታየበት መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ ፣ ነሃሴ 5 ፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ ) የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣው አዋጅ አፈፃፀም ከፍተኛ ክፍተት እየታየበት መሆኑ ተገለጸ።
 
ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉ የደቡብ፣ ሶማሌ እና ጋምቤላ ክልሎች የጤና ቢሮ ሃላፊዎች÷ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት የተላለፉ ውሳኔዎችን በማስፈፀም ረገድ በተለይም በክልሎች ከፍተኛ ክፍተት እየታየ ነው መሆኑን ገልጸዋል።
 
ህብረተሰቡ ከገባበት መዘናጋት ለማንቃት ፣ ሰፊ የላብራቶሪ ምርመራ ለማድረግ የንቅናቄ ስራ መጀመራቸውንም ነው ክልሎቹ ያስታወቁት።
 
የደቡብ ክልል ጤና ቢሮ ሃላፊ አቶ አቅናው ካውዛም በክልሉ የአዋጁ አፈፀጻም ላይ ክፍተት ሰፊ መሆኑን አንስተው ÷ ክልሉ ትናንት በይፋ በጀመረው የንቅናቄ ስራም የአዋጁ አፈጻፀም ላይ የታዪ ችግሮችን ማስተካከል ላይ ትኩረት ተደርጎ ይሰራል ብለዋል።
 
በደቡብ ክልል ከ320 በላይ ሰዎች የኮሮና ቫይረስ የተገኘባቸው ሲሆን÷ በአስከሬን ምርመራም 3 ሰዎች ቫይረሱ እንደተገኘባቸው መረጋገጡን የቢሮው ሃላፊ አቶ አቅናው ካውዛ ተናግረዋል።
 
ይህም በማህበረሰቡ ዘንድ ቫይረሱ እየተሰራጨ መሆኑን እንደሚያሳይ ያነሱት ሃላፊው÷ በክልሉ በየወሩ ከ10 የማይበልጥ ሰው በቫይረሱ ሲያዝ መቆየቱንና አሁን በሃምሌ ወር በ93 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ገልጸዋል።
 
ቫይረሱ ከዚህም የከፋ ቀውስ ያመጣል ተብሎ በሚጠበቅበት በዚህ ወቅት እየታየ ያለው የጥንቃቄ እርምጃ ግን የተገላቢጦሽ መሆኑን ሃላፊው ገልጸዋል።
 
በሶማሌ ክልል እና ጋምቤላ ክልል ያለው መዘናጋት አሳሳቢ መሆኑንም የክልሎቹ የጤና ቢሮ ሃላፊዎች ተናግረዋል።
 
የሶማሌ እና ጋምቤላ ክልሎች አሁንም ድንበር ከሚጋሩ ሀገራት በኩል በህገወጥ መንገድ የሚገቡ ሰዎች ስለመኖራቸው ያነሳሉ።
 
ይሁን እንጂ በሁለቱም ክልሎች በትራንስፖርት እና አገልግሎት መስጫዎች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛን ማድረግም ሆነ ርቀትን መጠበቅ ላይ የሚታየው አፈፃፀም እጅግ አንገብጋቢ ጉዳይ መሆኑን የሁለቱ ክልሎች ጤና ቢሮ ሃላፊዎች ተናግረዋል።
 
በሶማሌ ክልል እስከትናንት ድረስ 798 ሰዎች ቫይረሱ የተገኘባቸው ሲሆን÷የ21 ሰዎች ህይወት አልፏል።
በጋምቤላም እንዲሁ ባለፉት ሁለት ቀናት የላብራቶሪ ምርመራ
 
አገልግሎት ከማቆሙ በፊት ባለው ሪፖርት 628 ሰዎች ቫይረሱ የተገኘባቸው ሲሆን÷ 7 ሰዎች በወረርሽኙ ምክንያት ህይወታቸውን አጥተዋል።
 
ከ300 ሺህ በላይ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች የሚገኙበት የጋምቤላ ክልል፣ በካምፕ የሚኖሩ ስደተኞች እና የአካባቢዎቹ ማህበረሰብ ትስስር የኮቪድ 19ኝን ታሳቢ ያደረገ አይደለም ሲሉ የክልሉ ጤና ቢሮ ሃላፊ አቶ ካን ጋሏክ ገልጸዋል።
 
በፋሲካው ታደሰ
 
#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.