Fana: At a Speed of Life!

ለዓመቱ የተያዘው 5 ቢሊየን ችግኝ የመትከል እቅድ መሳካቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ገለፁ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 6፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በባህርዳር ከተማ በተካሄደው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ላይ ተሳትፈዋል።

በዚህ ወቅት ባደረጉት ንግግር ለዓመቱ የክረምት ወቅት የተያዘው 5 ቢሊየን ችግኝ የመትከል መርሃ ግብር በውቢቷ ሀዋሳ ከተማ ተጀምሮ በውቢቷ ባህርዳር ከተማ ተሳክቷል ብለዋል።

ባለፈው ዓመት 4 ቢሊየን ችግኝ ክረምቱን በሙሉ በተከናወነ መርሃ ግብር መተከሉን ያስታወቁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዘንድሮ 5 ቢሊየን ችግኝ ግን ክረምቱ አንዱ ወር ቀርቶት ማሳካት እንደተቻለ ተናግረዋል።

በመሆኑም እቅዱ ቀድሞ በመሳካቱ ተጨማሪ 200 ሚሊየን ችግኝ መዘጋጀቱን ነው የተናገሩት።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዓመቱን የችግኝ መትከል እቅድ በቁጥር ብቻ ሳይሆን በውጤትም የምናሳካው ይሆናል ሲሉ ነው የገለፁት።

ለቀጣዩ ዓመት በተመሳሳይ 6 ቢሊየን ችግኝ እንደሚዘጋጅ ያስታወቁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዘንድሮውም ሆነ ካለፈው ዓመት ለየት ባለ መልኩ ለጎረቤት ሀገራት 1 ቢሊየን ችግኝ ይዘጋጃልም ብለዋል።

በአራተኛው ዙርም ኢትዮጵያውያን በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የሚተክሉት ችግኝ 20 ቢሊየን እንደሚደርስም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።

20 ቢሊየን ችግኝ የመትከል እቅድ ስኬታማ በሚሆንበት ወቅትም የታላቁ የህዳሴ ግድብ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ሪባን የሚቆረጥ ይሆናልም ነው ያሉት።

ትላልቅ ፕሮጀክቶችን የማቀድ፣ የማለም እና የማሳካት እቅዳችን እያደገ ሲሄድ ኢትዮጵያ ወደ ብልፅግና ማማ ወጥታ የምናይበት ይሆናል ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጭቃ ሳንነካ የምናበልፅገው ሀገር እንደሌለ አውቆ፣ ችግር ሳንጋፈጥ የምንቀይረው ሀገር እንደሌለ አውቆ፣ በሽታው መፍረሱም በጭንቅላታችን መሆኑን አውቆ በጭንቅላት ውስጥ ያለውን ካንሰር በማፅዳት ይህችን ታላቅ ሀገር አንድነቷ እና ብልፅግናዋን ማረጋገጥ ከሁሉም የሚጠበቅ መሆኑን አውስተዋል።

በባህርዳር ከተማ በሚገኘው ቤዛዊት ተራራ በተካሄደው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን፣ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ እና ሌሎች የክልልና የፌደራል ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ተሳታፊ ሆነዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.