Fana: At a Speed of Life!

በጋምቤላ ክልል እየተገነባ የሚገኘው የፀሃይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት አፈፃፀም 74 ከመቶ ሲደርስ÷በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተገነባው የፀሃይ ሃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል

አዲስ አበባ፣ ነሀሴ 11፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በጋምቤላ ክልል በአኝዋክ ዞን እየተገነባ የሚገኘው የፀሃይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት አፈፃፀም 74 ከመቶ ሲደርስ÷ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተገነባው የፀሃይ ሃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል፡፡

በ5 ሺህ 950 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈው በጋምቤላ ክልል እየተገነባ የሚገኘው የፀሃይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት በ425 ሺህ 746 የአሜሪካ ዶላር ወጪ ሲ ኢቲ እና ኤን አር በተባለ የቻይና ኩባንያ እየተገነባ ይገኛል፡፡

ለፕሮጀክቱ እስካሁን 5 ነጥብ 9 ኪሎ ሜትር የመካከለኛ መስመር ዝርጋታ የተከናወነ ሲሆን ግንባታው ሲጠናቀቅ ከ175 ኪሎ ዋት በላይ ኃይል ማመንጨት የሚችል ነው ተብሏል፡፡

ፕሮጀክቱ ከ150 እስከ 200 ለሚጠጉ ደንበኞች እንዲሁም የተለያዩ የመንግስት ተቋማት አገልግሎት መስጠት እንደሚችልም ታውቋል፡፡

የፀሃይ ኃይል ማመንጫው ከአንድ ወር በኋላ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

በተያያዘ ዜና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከ25 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው የፀሃይ ሃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ፡፡

ፕሮጀክቱ የካቲት 2011 ዓ.ም ግንባታው የተጀመረ ሲሆን 25 ሚሊየን 936 ሺህ 603 ብር ወጪ ተደርጎበታል ነው የተባለው፡፡

የፕሮጀክቱ ስራ የማከፋፈያ ጣቢያ ግንባታ ሲ ኢቲ ኮንሰርተም በተባለ የቻይና ኩባንያ ሲሰራ የማሰራጫ ግንባታው ደግሞ በሀገር አቀፍ ኤሌክትሪክ አቅርቦት ፕሮግራም የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሪጅን ጽህፈት ቤት ተከናውኗል፡፡

የሃይል ማከፋፈያ ጣቢያው 275 ኪሎ ዋት ሀይል የማመንጨት አቅም ያለው መሆኑም ታውቋል፡፡

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.