Fana: At a Speed of Life!

የደብረ ታቦር በዓል( ቡሄ) በደብረ ታቦር ከተማ እየተከበረ ነው

አዲስ አበባ ፣ ነሀሴ 13 ፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የደብረ ታቦር በዓል( ቡሄ) በደብረ ታቦር ከተማ በዛሬው ዕለት እየተከበረ ይገኛል።

በዓሉ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን አማንያን ዘንድ ኢየሱስ ክርስቶስ በታቦር ተራራ ብርሃነ መለኮቱን የገለጠበትን በማሰብ በየአመቱ ነሃሴ 13 ይከበራል።

የደብረ ታቦር በዓል (ቡሄ) በበዓሉ ስያሜ በምትጠራው ጥንታዊቷ የደብረታቦር ከተማ ኢየሱስ ቤተክርስትያን ነው እየተከበረ የሚገኘው።

የቡሄ በዓል ከሃይማኖታዊ አከባበሩ ባለፈ ህዝባዊ በዓልም ሲሆን አሮጌውን አመት ለመጨረስ አዲሱን አመት ለመቀበል ዝግጅት በሚደረግበት ወቅት የሚከበር በመሆኑ ተስፋን ይዞ የሚመጣ በዓል መሆኑ በብዙዎች ዘንድ ይነገራል።

በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ሕጻናት በዓሉ ከመድረሱ በፊት ቀደም ብለው ጅራፍ ሲገምዱና ሲያጮሁ ይቆያሉ።

በደብረ ታቦር ከተማ መከበሩ የከተማዋን የጎብኚዎች ቁጥር በማሳደግ ኢኮኖሚውን ከፍ ለማድረግ አስተዋጽኦው የላቀ መሆኑም ተነግሯል።

በተለይ የቡሄ በዓልና መሰል በዓላት የሰዎችን ግንኙነት ከፍ የሚያደርጉ በመሆኑ ወንድማማችነትን ለማጠናከር፣ አብሮ መኖርን ለማሳደግ፣ አንድነትን ለማጠናከርና ፍቅርንም ለማጎልበት የጎላ ጠቀሜታ እንዳለው ተጠቁሟል።

በሃይማኖት ኢያሱ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.