Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ ለ10 የማዕድን ምርመራ እና 2 የማዕድን ምርት ፈቃዶች ተሰጡ

አዲስ አበባ ፣ ነሀሴ 13 ፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የማዕድናት ፍለጋ እና ልማት ለማካሄድ ፈቃድ ለጠየቁና የፈቃድ መውሰጃ መስፈርቶችን አሟልተው ለቀረቡ ለ12 የማዕድን ኩባንያዎች ፈቃድ መስጠቱን የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ በዛሬው ዕለት ባወጣው መግለጫ ሁለቱ የምርት ፈቃዶች ሲሆኑ አስሩ የምርመራ ፈቃዶች መሆናቸውን ገልጿል፡፡

የምርት ፈቃድ የተሰጣቸው የባዛልት እና የዕምነበረድ ማዕድን ምርት ሲሆኑ ሌሎች 10 ኩባንያዎች ደግሞ በደለል ወርቅ፣ ወርቅና መሰል ማዕድናት፣ ብረት፣ ማንጋነዝ፣ ክሮማይት፣ ብር እና ጀም ስቶን ማዕድናት ምርመራዎች ናቸው፡፡

ሁለቱ የምርት ፈቃዶች ለኢንቨስትመንት 270 ሚሊየን 186 ሺህ ብር ካፒታል ያስመዘገቡ ሲሆን ለ187 ዜጎች የስራ ዕድል እንደሚፈጥሩ ሚኒስቴሩ አስታውቋል።

በተመሳሳይ የምርመራ ፈቃዶች ደግሞ 131 ሚሊየን 935 ሺህ ብር የተመዘገበ ካፒታል እና በምርመራ ወቅት በድምሩ ለ293 ዜጎች የስራ ዕድል የሚፈጥሩ ናቸው።

የምርመራ ሂደታቸውን በስኬት አጠናቀው ወደ ስራ ሲገቡም ከስራ ዕድል ፈጠራ እስከ ውጭ ምንዛሬ ግኝትና ማዳን ጉልህ አስተዋፅኦ ያበረክታሉ ነው የተባለው፡፡

የምርመራ ፈቃድ የውል ስምምነት ፊርማው ከተፈረመበት ቀን ጀምሮ እንደ የፍቃዱ ዓይነት ከ1 ዓመት እስከ 3 ዓመት የሚፀና ሆኖ የፈቃድ ዘመኑም ሲጠናቀቅ በባለፈቃዱ ጥያቄ መሠረትና ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሲያምንበት ሊታደስ የሚችል መሆኑም ተጠቁሟል፡፡

ዛሬ ፈቃድ የወሰዱ ኩባንያዎች የምርትም ሆነ የምርመራ ሥራቸውን ሲያከናውኑ በፌደራልና በክልል የማዕድን አዋጆች፣ ደንቦችና መመሪያዎችን መሰረት አድርጎ በጥንቃቄ በትጋትና ቅልጥፍና በተሞላበት ሁኔታ በማዕድን ኢንዱስትሪው ዘርፍ ተቀባይነት ባለው የአሰራር ዘዴ ለማከናወን በስምምነቱ ውስጥ ተካቷል።

እንዲሁም ተመጣጣኝ ዕውቀት፣ ችሎታና ልምድ ላላቸው ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ቅድሚያ የስራ ዕድል ለመስጠትና ለስራው አስፈላጊ የሆነውን ሥልጠና የመስጠት ግዴታ አለባቸው ተብሏል፡፡

የስምምነቶቹን ፈቃድ የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትር ዲኤታ ወይዘሮ ስመኝ ውቤ ከፈቃድ ወሳጅ ኩባንያዎች ዋና ስራ አስፈጻሚዎች ጋር ተፈራርመዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.