ብሪታኒያውያን ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት በስፋት እንዲሳተፉ ጥሪ ቀረበ
አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 8፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አክሊሉ ሃይለሚካኤል ከብሪታኒያ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ፊሊፕ ፓርሃማን ጋር ተወያዩ፡፡
ሁለቱ ወገኖች በነበራቸው ውይይት በቀጣዩ ጥር ወር 2012 ዓም በለንደን የሚካሄደውን የአፍሪካ ብሪታኒያ የኢንቨስትመንት ጉባኤ በተመለከተ ውይይት አድርገዋል፡፡
ጉባኤው የአፍሪካ መሪዎችን፣ የቢዝነስ አካላትንና ዓለም አቀፍ ተቋማትን ፊት ለፊት በማገናኘት አፍሪካንና ብሪታኒያ በኢንቨስትመንት እና በንግድ በማስተሳሰር የስራ እድል ለመፍጠር ያለመ መሆኑን ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ፊሊፕ በዚህ ወቅት ገልጸዋል።
አምባሳደሩ በጉባኤው ኢትዮጵያ እንድትሳተፍም ግብዣ አቅርበዋል።
ዶክተር አክሊሉ ሃይለሚካኤል በበኩላቸው መሰል ጉባኤዎች የኢንቨስትመንት ማነቆዎችን ለመፍታት እና ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት ወሳኝ ሚና እንደሚጫወቱ በማስታውስ ኢትዮጵያ በጉባኤው እንድትሳተፍ ስለቀረበው ግብዣ አመስግነዋል።
በአትዮጵያ ስላሉ ምቹ ኢንቨስትመንት አማራጮችም ገለጻና ማብራሪያ በመስጠት ብሪታኒያዊያን ባለሀብቶች በስፋት እንዲሳተፉ ዶክተር አክሊሉ በዚህ ወቅት ጥሪ ማቅረባቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡