የፖለቲካ ፓርቲዎች ካለፉ ታሪኮች እና ትርክቶች ቁዘማ ወጥተው ለሀገር ሰላም እና ለህዝቦች አንድነት ሊሰሩ እንደሚገባ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ታህሳስ 8፣2012(ኤፍ.ቢ.ሲ) የፖለቲካ ፓርቲዎች ካለፉ ታሪኮች በመማር ለሀገር ሰላም እና ለህዝቦች አንድነት ሊሰሩ እንደሚገባ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ያነጋገራቸው የታሪክ ምሁራንና ፖለቲከኞች ገለጹ።
በሃረማያ ዩኒቨርሲቲ መምህርና የታሪክ ምሁሩ ረዳት ፕሮፌሰር ሲሳይ አውግቸው፥ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያለፉ ታሪኮችንና ትርክቶችን የርዕዮት አለም አካል አድርገዉ መንቀሳቀሳቸውን በማቆም የፖለቲካ ትኩሳት የሚያደርሰዉን አሉታዊ ተጽዕኖ መከላከል እንደሚገባቸው ጠቁመዋል።
ፓርቲዎች ካለፉ ታሪኮች ሊማሩ ይገባል ያሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ፥ ለሰላም እና ሀገራዊ አንድነት የሚጠበቅባቸውን ሃላፊነት በተገቢው ሁኔታ መወጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
የአማራ ማህበራዊ ራዕይ ግንባር ሊቀመንበር አቶ ስዩም መንገሻ እና የመድረክ ፓርቲ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና በበኩላቸው፥ በሀገሪቱ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሃሳብ ልዕልና ላይ የተመሰረተ ፖሊሲና ስትራቴጂን በመንደፍ የህዝብን ችግሮች መፍታት ላይ ሊያተኩሩ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
በመነጋገርና ተቀራርቦ በመስራት መርህ ላይ የተመሰረተ ዴሞክራሲ ለሰላም ካለው አበርክቶ አንጻር ፖለቲካ ፓርቲዎች ጠንካራ ስራ ሊሰሩ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
በአወል አበራ