Fana: At a Speed of Life!

በሰው ህይወትና ንብረት ላይ ቁማር ከሚጫወት የፖለቲካ አካሄድ መውጣት ይገባል – የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት

አዲስ አበባ ፣ ነሃሴ 16 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በሰው ህይወትና ንብረት ላይ ቁማር ከሚጫወት የፖለቲካ አካሄድ በመውጣት የኢትዮጵያን ደህንነታዊ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ማረጋገጥ እንደሚገባ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አሳሰበ፡፡

ምክር ቤቱ በብሄራዊ መግባባት ዙሪያ ውይይት እያደረገ ነው፡፡

በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን እየተካሄደ ባለው ውይይት መክፈቻ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ሙሳ አደም፤ እንደ ሃገር በአንድነት ለመቆም መንግሥት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ህዝቡ የሚጠበቅባቸውን ሃገራዊ ሚና እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡

ፓርቲዎች መቀራረብና የሃሳብ መሸናነፍን ያስቀደመ የፖለቲካ ባህል በማዳበር ችግሮቻቸውን በጋራ የሚፈቱ መሆን እንደሚገባቸውም አንስተዋል፡፡

“ያለችን አንድ ሃገር ናት” ያሉት ሰብሳቢው፤ መንግሥት የዜጎችን ህይወትና ንብረት ከጥፋትና ውድመት የሚታደግ የህግ የበላይነትን ከማረጋገጥ ጎን ለጎን የዜጎችን መንግሥትን በሃሳብና በሰላማዊ ሰልፍ የመቃወም መብትንም ማክበር አለበትም ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል ህዝቡ የእነዚህን የፖለቲካ ወገኖች አቋምና አቅም በሚገባ በመረዳት በሃገራዊ አንድነቱ ላይ አደጋ የሚደቅን ፖለቲካዊ ሴራ መፈፀሚያ ከመሆን መቆጠብ እንደሚገባውም አመልክተዋል፡፡

በችግሮች ጊዜም ቆም ብሎ በማሰብ በጥላቻ ፖለቲካ ትርክትና ግፊት ቋሚ ጎረቤቱንና ንብረቱን ከማውደም እንዲቆጠብ ጠይቀዋል ሰብሳቢው፡፡

“ይህ ሲሆን ብቻ ነው ብሄራዊ መግባባትን በኢትዮጵያ እውን ማድረግ የሚቻለውም” ብለዋል አቶ ሙሳ በንግግራቸው፡፡

ለአሳዳጅ ተሳዳጅ የፖለቲካ ፍፃሜ ለማበጀት እንደሚሰራ የገለፀው ምክር ቤቱ፤ ከሁሉ በፊት በሰው ህይወትና ንብረት ላይ ቁማር ከሚጫወት የፖለቲካ ስርአት መውጣት እንደሚያስፈልግም በፅኑ አሳስቧል፡፡

ውይይቱን የመሩት ዶክተር አረጋዊ በርሄ፣ ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና፣ ሻምበል አማን ኡስማን እና አቶ የሺዋስ አሰፋ ሲሆኑ፤ ከኢትዮጵያ የምስረታ ዘመን እስከ ስርአቶች ዝርጋታ ታሪካዊ – ጥናታዊ የመነሻ ሃሳብ በፕሮፌሰር መረራ አማካይነት ቀርቦ በፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ውይይት እየተካሄደበት ነው፡፡

በሶዶ ለማ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.