Fana: At a Speed of Life!

ወጣቶች ከአባቶች በብዙ ድካም የተረከቧትን ሃገር ጠብቀው እና አልምተው ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ ይገባቸዋል – ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ

አዲስ አበባ ፣ ነሃሴ 16 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ወጣቶች ከአባቶች በብዙ ድካም የተረከቧትን ሃገራቸውን ጠብቀው እና አልምተው ለቀጣዩ ትውልድ እንዲያስተላልፉ ጥሪ አቀረቡ፡፡

የዓለም የወጣቶች ቀን በኢትዮጵያ የወጣቶች ተሳትፎ ለኢትዮጵያ ብልጽግና በሚል መሪ ቃል እየተከበረ ነው፡፡

በበዓሉ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ወጣቶች ሃገራቸውን ጠብቀውና አልምተው ለቀጣዩ ትውልድ እንዲያስተላልፉ ጠይቀዋል፡፡

ፕሬዚዳንቷ በመልዕክታቸው የኢትዮጵያ ነገ፣ የኢትዮጵያ ብሩህ ቀን በእናንተ በወጣቶች ውስጥ አለ ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ በአሁኑ ሰአት በራሱ ወገን ላይ አሰቃቂ ጥቃት የሚፈጽም ወጣት እንዳለ ሁሉ ለሃገራቸው ልማት ቀን ከሌት የሚደክሙትን ማየታችን ደስታ ይሰጣል፤ የኢትዮጵያን ነገም ብሩህ ያደርገዋል ብለን እናምናለንም ነው ያሉት፡፡

የሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስትሯ ወይዘሮ ፊልሰን አብዱላሂ በበኩላቸው ወጣቶች በወጣትነት እድሜያቸው ለራሳቸውና ለሃገራቸው ብዙ የሚሰሩበት በመሆኑ ወጣትነታቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙበት ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥም ወጣቶች በቁርጠኝት እንዲሰሩ መልዕክት አስተላልዋል፡፡

በኢትዮጵያ ሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር አዘጋጅነት እየተከበረ ባለው በዓል ለህዳሴ ግድብ በተለየ መልኩ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ወጣቶች እውቅና ይሰጣል፡፡

በተለይም በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ተደራሽ በሆነ መልኩ በህዳሴው ግድብ ላይ የኢትዮጵያን አቋም እና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት በተለያዩ ቋንቋዎች ሲያንጸባርቁ የነበሩ ወጣቶች እውቅና ይሰጣቸዋል ተብሏል፡፡

ከተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች የመጡ ወጣቶችም በመርሃ ግብሩ ላይ እየተሳተፉ ነው፡፡

በለይኩን ዓለም

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.