ሲሜንቶ ለመግዛት ዘጠኝ ወር ወረፋ እንደሚጠብቁ የአማራ ክልል የስሚንቶ ነጋዴዎች ገለፁ
አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 8 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የአማራ ክልል ንግድና ገቢያ ልማት ቢሮ በሲሜንቶ ምርት ግብይት ላይ በሚስተዋሉ ችግሮች ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል።
በውይይቱ የፌዴራል ንግድ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ እሽቴ አስፋው ፣ የአማራ ክልል ንግድና ገቢያ ልማት ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ተዋቸው ወርቁ ፣ የሲሜንቶ ፋብሪካ ሃላፊዎችና የአማራ ክልል ሲሜንቶ ነጋዴዎች ተገኝተዋል።
ነጋዴዎች በውይይቱ ላይ ከዋጋ መጨመሩ ጋር ተያይዞ ሲሜንቶ ለመግዛት ክፍያ ከፍለው ዘጠኝ ወር እንደሚጠብቁ ነው የገለፁት።
በውይይቱ ላይ የክልሉ ንግድና ገቢያ ልማት ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ተዋቸው ወርቁ ባቀረቡት ጥናታዊ ፅሁፍ የሲሜንቶ ዋጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን አንስተዋል።
በጥናታዊ ፅሁፋቸው ሰባት የሚሆኑ ችግሮች ለሲሜንቶ ዋጋ መጨመር ምክንያቶች ቢኖርም ዋና ዋናዎቹ ግን የንግድ አሻጥር የደላሎች መበራከትና የንግድ ስርአቱ በጥሬ ገንዘብ መሆናቸው ነው የገለፁት።
ከፋብሪካ የአንድ ከረጢት ሲሜንቶ ዋጋ 214 እስከ 242 ብር ቢሸጥም ለተጠቃሚው 305 ብር መሸጥ እያለበት 450 ብር ድረስ እንደሚሽጥ ነው በፅሁፋቸው ያነሱት፡፡
የፌዴራል ንግድ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ እሸቴ አስፋው በሲሜንቶ ግብይት የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከክልሎችና ከሲሜንቶ ፋብሪካዎች ጋር በቅርበት እንደሚሰራ ተናግረዋል።
በጥሬ ገንዘብ የነበረውን የግብይት በባንክ እንዲሆን እና እስከ ዘጠኝ ወር ይወስድ የነበረውን የግዥ ወረፋ ከ15 ቀን እስከ 3 ወር እንዲሆን ከፋብሪካ ሃላፊዎች ጋር ስምምነት ላይ መደረሱን ገልፀዋል፡፡
ሚኒስትር ዴኤታው አቶ እሽቴ አስፋው አክለው በንግድ ሚኒስቴር የተቋቋመ ግብረ ሃይሉ መኖሩን በመግለፅ ከዚህ በኋላ የማይቋረጥ ክትትልና ቁጥጥር እንደሚደርግ ተናግረዋል፡፡
የዳንጎቴ የስሚንቶ ፋብሪካ ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ መስፍን አበራ ችግሮችን ለመፍታት የበኩላችን ተናግረዋል፡፡
በናትናኤል ጥጋቡ