Fana: At a Speed of Life!

ወ/ሮ ሂሩት በእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ምክትል ዳይሬክተር ጄኔራል ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 9፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሂሩት ዘመነ በእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ምክትል ዳይሬክተር ጄኔራል ከሆኑት አምባሳደር እያንት ሽሌይን ጋር ተወያዩ።

ወይዘሮ ሂሩት ዘመነ አምባሳደር እያንት ሽሌይን በትናንትናው እለት በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው መወያየታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት መረጃ ያመለክታል።

ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሂሩት በዚህ ወቅት እንደገለጹት፥ የኢትዮጵያና የእስራኤል ግንኙነት በጠንካራ መሰረት ላይ የተገነባ ነው ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በእስራኤል ይፋዊ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ሁለቱ ሀገራት በሳይበር ደህንነት፣ በዘመናዊ ግብርና እንዲሁም በዓሳ ምርት ዙሪያ የተፈራረሟቸውን ስምምነቶች ከዳር ለማድረስ በኢትዮጵያ በኩል የተከናወኑ ተግባራትን በተመለከተ አብራርተዋል።

አምባሳደር እያንት ሽሌይን በበኩላቸው፥ በኢትዮጵያና በእስራኤል መካከል ያለው ግንኙነት ታሪካዊና በጠንካራ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት የታገዘ ነው ብለዋል።

እስራኤል በውሃ አጠቃቀም ዙሪያ ያላትን ሰፊ ልምድ ለኢትዮጵያ ለማካፈልም ዝግጁ መሆኗን ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በእስራኤል ጉብኝት ባደረጉት ወቅት የተፈረሙ ስምምነቶች ወደ ተግባር እንዲቀየሩ እስራኤል ቁርጠኛ መሆኗን በመግለፅ፤ በጉዳዩ ላይ ዝርዝር ጥናት የሚያደርጉ የእስራኤል ባለሙያዎች በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጡ ገልፀዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.