በእነ አቶ ጃዋር መሐመድ መዝገብ ቀሪ ምስክሮችን ለመስማት ለነሐሴ 20 ቀን ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጠ
አዲስ አበባ ፣ ነሃሴ 18 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌደራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ተረኛ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ተረኛ ችሎት አቶ ጃዋር መሐመድን ጨምሮ ስምንት ተጠርጣሪዎች ላይ በባለፈው ቀጠሮ በተጀመረ የዐቃቤ ህግ የቅድመ ምርመራ ምስክር ዛሬ ቀጥሎ የአንድ ምስክር ቃል ተሰምቷል።
ፍርድ ቤቱ ባለፈው ቀጠሮ ዐቃቤ ሕግ እና የተጠርጣሪ ጠበቆች ባቀረቧቸው አቤቱታዎች ላይ ትዕዛዝ ሰጥቷል።
አቶ ጃዋር እና አቶ በቀለ ገርባ ያለ ፈቃዳችን ፎቶግራፍ እና ቪዲዮ እየተቀረጽን በመገናኛ ብዙሃን እየቀረበ ስለሆነ ትዕዛዝ ይሰጥልን ሲሉ ባቀረቡት አቤቱታ ላይ ፍርድ ቤቱ ያለ ተጠርጣሪዎቹ ፈቃድ ለዘገባ ፎቷቸውንና ተንቀሳቃሽ ምስል አንስተው ወይም ቀርጸው መጠቀማቸው፤ የተጠርጣሪዎችን ንጹህ ሆነው የመገመት መብታቸውን ይጋፋል ሲል ፎቷቸውን ወይም ምስላቸውን በቪዲዮ ቀርጸው እንዳይጠቀሙ ሲል ትዕዛዝ ሰጥቷል።
በችሎት ቤተሰቦቻችን ይታደሙልን ለሚለው አቤቱታቸው ፍርድ ቤቱ ኮቪድ-19ን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ከአራት ያልበለጡ የተጠርጣሪ ቤተሰቦች ችሎቱን እንዲታደሙ አዟል።
ከሃይማኖት አባቶቻቸው እና ከጠበቆቻቸው ጋር ለ40 ደቂቃ ያህል ተገናኝተው እንዲያወሩም ችሎቱ ትዕዛዝ አስተላልፏል።
መለሰ ድሪብሳ የሚባል ተጠርጣሪም ከቤተሰብ ምግብ እና ልብስ ይግባልኝ ሲል ባቀረበው አቤቱታ ላይም ፍርድ ቤቱ ከቤተሰቦቹ ምግብ እንዲገባለት እና በስልክም እንዲያገኛቸው ብሏል።
የተጠርጣሪ ጠበቆች በችሎቱ ተንቀሳቃሽ ስልክ ይዘን እንዳንገባ ተከልክለን ለዐቃቤ ሕግ መፈቀዱ ተገቢ አይደለም በማለት ያቀረቡትን አቤቱታ የመረመረው ችሎቱ ዐቃቤ ሕግም ተንቀሳቃሽ ስልክ ይዞ ወደ ችሎት እንዳይገባ አዟል።
አቶ ጃዋር መሀመድ የባንክ አካውንታችንና ንብረታችን ታግዷል በማለት እግዱ እንዲነሳላቸው ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡
ፍርድ ቤቱም በዚህ መዝገብ ምንም ዓይነት ንብረትም ሆነ የባንክ አካውንትን አላገድኩም፤ ከጠበቆቻችሁ ጋር በመነጋገር ያገደውን አካል መጠየቅ ትችላላችሁ በማለት ምላሽ ሰጥቷል፡፡
አቶ በቀለ ገርባ በመገናኛ ብዙሃን ቃለ መጠይቅ እየተደረገ ዘመቻ እየተደረገብን ነው ፍርድ ቤቱ ጥፋተኛ ብሎ እስካልፈረደብን ድረስ ንጹህ ሆነን የመገመት መብታችን ይከበር ብለው ላቀረቡት አቤቱታ ፍርድ ቤቱ አስቀድሞ በመገናኛ ብዙሃን ላይ ትዕዛዝ መስጠቱን አብራርቷል።
ፍርድ ቤቱ ይህንና ሌሎች ትዕዛዛትን በማስተላለፍ ዐቃቤ ህግ ካቀረባቸው ምስክሮች መካከል የአንድን ምስክር ከ3 ሰዓታት በላይ የፈጀ የምስክርነት ቃል አድምጦ የዛሬውን ውሎ አጠናቋል፡፡
የሌሎችን ምስክሮች ቃል ለመስማትም ለነሃሴ 20 ቀን 2012 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
በታሪክ አዱኛ