Fana: At a Speed of Life!

ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ከቻይና መንግስት ገቢዎች አስተዳደር ሃላፊ ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 9፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በገቢዎች ሚኒስትር ወይዘሮ አዳነች አቤቤ የተመራ ከፍተኛ የመንግስት ልዑካን ቡድን በቻይና ጉብኝት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡

በጉብኝቱ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ከቻይና መንግስት ገቢዎች አስተዳደር ሃላፊ ዋንግ ጁ ጋር በቤጂንግ ውይይት አድርገዋል፡፡

የስራ ሃላፊዎቹ በውይይታቸው ሁለቱ ሀገራት በገቢ አሰባሰብ ላይ ተባብረው ለመስራት፣ ልምድ ለመለዋወጥ፣ በቴክኖሎጂ እና በሰው ኃይል አቅም ግንባታ ዘርፍ ለመደጋገፍ መግባባት ላይ ደርሰዋል።

ሚኒስትሯ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በፍጥነት እያደጉ ካሉ ኢኮኖሚዎች አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፥ የቻይና ባለሃብቶች ተሳትፎ በየጊዜው መጨመሩ ለሁለቱ ሀገራት ጠንካራ ወዳጅነት መገለጫ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከምታስገባው የውጭ ምርት መጠን ከ72 በመቶ በላይ የሚሆነው ከቻይና መሆኑን ጠቅሰው፥ ኢትዮጵያም ባለፉት አምስት አመታት ወደ ቻይና 1 ነጥብ 1 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ዋጋ ያላቸውን ምርትች መላኳን ገልጸዋል።

በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ ያለውን ኢኮኖሚ ለመደገፍና የተሳለጠ አገልግሎት ለመስጠት የገቢ አሰባሰብና ግብር አስተዳደርን ማዘመን አስፈላጊ መሆኑንም ተናግረዋል።

ሚኒስትሯ የቻይና ኤርፖርቶች ጉምሩክ አሰራርን የጎበኙ ሲሆን ኢትዮጵያም የዘመነና በቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራር እንዲኖራት እየሠራች መሆኑን አስረድተዋል።

አያይዘውም ኢትጵያና ቻይና ያላቸውን የቆየና ጠንካራ ግንኙነት ግምት ውስጥ ያስገባ ድጋፍ እንዲደረግም ጠይቀዋል።

ዋንግ ጁን በበኩላቸው የኢትዮጵያና ቻይና ትብብር በደቡብ ደቡብ ትብብር፣ በቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ እንዲሁም በሁለትዮሽ ትብብር መስኮች የቻይና አፍሪካ ግንኙነት የትብብር አርዓያ ተደርጎ እንደሚወሰድ ጠቅሰዋል፡፡

የኢትዮጵያን የገቢ አሰባሰብና ግብር አስተዳደር ወደ ዲጂታል በመቀየሩና በማዘመኑ ሂደት ቻይና ሙሉ ድጋፍ ታደርጋለች ማለታቸውን ከገቢዎች ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.