Fana: At a Speed of Life!

በዩኒቨርሲቲዎች የሚከሰቱ ግጭቶች ከትምህርት ስርዓቱ፣ ከአስተዳደር ሁኔታዎችና ከአገሪቱ የፖለቲካ እውነታ ጋር የተያያዙ መሆናቸው ተመለከተ

አዲስ አበባ ፣ ነሀሴ 19 ፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (ካርድ) የጥናት ውጤትን መሰረት አድርጎ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ግጭት መንስዔና ጉዳቶች አስመልክቶ ዓመታዊ መግለጫ አውጥቷል።

ካርድ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ ÷ በ2012 የትምህርት ዘመን በኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የተከሰቱ ግጭቶችን እና ያደረሱትን ጉዳት የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (ካርድ) ሲከታተል መቆየቱን አስታውቋል።

በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መካከል የሚከሰቱ ግጭቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀቡ መሔዳቸውን በመረዳት ካርድ የተለያዩ ቅድመ ዳሰሳዎችን እና ውይይቶችን ማካሄዱን ገልጿል።

በውጤቱም የችግሮቹ ምንጮች ከትምህርት ስርዓቱ፣ ከአስተዳደር ሁኔታዎች እና ከአገሪቱ የፖለቲካ እውነታ ጋር የተያያዘ መሆኑን የሚያመለክቱ መረጃዎችን ማግኘቱን ገልጿል።

በዩኒቨርስቲዎች በነበረው ግጭትም 12 ተማሪዎች ለሞት መዳረጋቸውን፣ ከ58 ተማሪዎች በላይ ቀላልና ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው መሆኑን እና 28 ዩኒቨርሲቲዎች ቀላል እና ከባድ ግጭቶች በማስተናገዳቸው የትምህርት ሒደቱ መስተጓጎል ማጋጠሙን መግለጫው አመልቷል።

በዚሁ የትምህርት ዓመት በጥቅምት 30 ቀን 2012 በወልዲያ በተከሰተ ግጭት የሁለት ተማሪዎች ሕይወት ያለፈ ሲሆን÷ ይህንን ተከትሎ በህዳር ወር 16 ያህል ዩኒቨርሲቲዎች ግጭቶችን አስተናግደዋል ነው ያለው።

ግጭቶቹ የብሔር መልክ ያላቸው ሲሆን ማኅበራዊ ሚዲያዎች በሐሰተኛ መረጃዎች ግጭቶቹን የማቀጣጠል ሚና እንደተጫወቱም ገልጿል።

ካርድ ዓመቱ በግጭቶቹ ምክንያት ትምህርት የተስተጓጎለበትና የተማሪዎች ደኅንነት አደጋ ላይ የወደቀበት ሆኖ አልፏል ነው ያለው።

ሆኖም ካርድ ባለው ውሱን አቅም ስለግጭቶቹ በመገናኛ ብዙኀን የተደረጉትን ዘገባዎችን በመከታተል ለተጨማሪ ምርመራ እና የመከላከል ሥራ እንዲያግዝ ጥቅል ዓመታዊ መግለጫ በዩኒቨርሲቲዎች ግጭት ጉዳይ ማዘጋጀቱን ገልጿል።

ማዕከሉ ሁሉም የባለ ድርሻ አካላት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ግጭት ለመቅረፍ በትብብር እንዲሠሩ ጥሪ አቅርቧል።

#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.