Fana: At a Speed of Life!

የደቡብ ክልል የገበታ ለሀገር ፕሮጀክትን ለመደገፍ ዝግጅት እያደረገ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ ፣ ነሀሴ 19 ፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የገበታ ለሀገር ፕሮጀክትን በገንዘብም ሆነ በመንፈስ ለመደገፍ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ሰሞኑን የኮይሻ፣ የጎርጎራና የወንጪ ሀይቅ አካባቢን በህብረተሰብ ተሳትፎ በማልማት አካባቢዎቹን ተመራጭ የቱሪስት መድረሻ ለማድረግ የሚያስችል ፕሮጀክት ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል ።

ይህንን ተከትሎም በየደረጃው ያሉ የደቡብ ክልል ማዕከል አመራሮች የአንድ ወር ደመወዛቸውን መለገሳቸው ተጠቁሟል።

የደቡብ ክልል ማዕከል አመራሮች በጠቅላይ ሚኒስትሩ ፕሮጀክት ዙሪያ ውይይት ባካሄዱበት ወቅት ÷ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ እርስቱ ይርዳ የገበታ ለሀገር ፕሮጀክትን በገንዘብም ሆነ በመንፈስ ለመደገፍ የክልሉ ህዝብና መንግስት ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል ።

በገበታ ለሸገር የታየው አዲስ አስተሳሰብና እይታ ድንቅ ውጤት ወደ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ፕሮጀክት ” ገበታ ለሀገር” መሸጋገሩ ሁሉንም የሚያስደስት ነው ሲሉም አክለዋል።

የኮይሻ ፕሮጀክት በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ሁሉንም የክልሉ ህዝብ በሁለንተናዊ መልኩ ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው ያሉት አቶ ርስቱ ለዚህም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሊመሰገኑ ይገባል ሲሉም ተናግረዋል ።

የኮይሻ ፕሮጀክት የጨበራ ጩርጩራ ብሄራዊ ፓርክን፣የግቤ 3 እና ኮይሻ ግድቦችና የአካባቢው ተፈጥሯዊ መስህቦችን የሚያስተሳስር በመሆኑ ፋይዳው ከፍተኛ እንደሆነ ተነግሯል።

በዚህም ፕሮጀክቱ የሀገር ገቢን ከማሳደግ ባለፈ ለአካባቢው ህዝብ በተለየ ሁኔታ ደግሞ የቱሪዝም ፍሰትን በመጨመርና ትርጉም ያለው የስራ እድል በመፍጠር ረገድ ድርሻው ከፍተኛ መሆኑንም ጠቁመዋል ።

ህዝቡም የበኩሉን አሻራ እንዲያሳርፍም ጥሪ አቅርበዋል።
የደቡብ ክልል ባህል፣ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ሃላፊ አቶ ስንታየሁ ወልደሚካኤል ÷ የኮይሻ ፕሮጀክትን ስኬታማ ለማድረግ ህዝቡን በማስተባበር 1 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ እቅድ መያዙን ተናግረዋል።

ለዚህም በክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር የሚመራ አብይ ኮሚቴ ተዋቅሮ ስራዎችን የሚያስተባብር ይሆናል ነው የተባለው።

የሚዋቀሩት ኮሚቴዎችም ህዝብ የራሱን ድርሻ እንዲያበረክት የማድረግ ፣ የአካባቢውን የቱሪዝም እምቅ የማስተዋወቅና በአካባቢው አስተማማኝ ሰላምና ጸጥታ የማስፈን ግቦችን ይዘው እንደሚንቀሳቀሱ አቶ ስንታየሁ መናገራቸውን ከደቡብ ክልል የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.